“…የተሰጠኝን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ካለኝ ፍላጎት የመጣ ነው” አሥራት ቱንጆ

በኢትዮጵያ ቡና መለያ መጫወት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ አስደናቂ ብቃቱን እያሳየ ከሚገኘው እና የአስተዋፅኦውን ያህል ካልተዘመረለት ታታሪው አሥራት ቱንጆ ጋር ቆይታ አድርገናል።

ከጅማ አባ ጅፋር ወደ ቡናማዎቹ ቤት ከመጣ ጀምሮ እርሱ ከለመደው ቦታ ውጭ በተለያዩ ቦታዎች ተጫውቷል። ሁሌም የሚሰጠውን ሚና በመተግበር ወደር የማይገኝለት ይህ ታታሪ ተጫዋች በዘንድሮ ዓመት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ውድድር በሁሉም ጨዋታዎች ለማለት በሚያስችል መልኩ በግራ ተከላካይነት ተሰልፎ ወደፊት በመሄድ በማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ የሚያደርገው ተሳትፎ አስደናቂ ነው። በዛሬው ዕለትም ሲዳማ ቡና ላይ የማሳረጊያውን አምስተኛ ጎል ከማስቆጠሩ ባሻገር ለአንድ ጎል መቆጠር አስተዋፆኦ አድርጓል። ይህ ብዙ ያልተዘመረለትን ኮከብ ከጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ አግኝተነው ስለወቅታዊ አቋሙ ተከታዩን ምላሽ ሰጥቶናል።

” የዛሬው ጨዋታ ጥሩ ነበር። ሦስት ነጥብ ያስፈልገን ነበር። ይህን ለማሳካት የተቻለንን አድርገናል። እንደ ቡድን አሰልጣኛችን የነገረንን አድርገን ወጥተናል። እኔም ለጎል የሚሆን እድል ከመፈጠሬ በተጨማሪ ጎል በማስቆጠሬ ደስተኛ ነኝ።

“ብዙ ዕይታ ውስጥ አለመግባቴ እኔም ግራ የሚያጋባኝ ነገር ነው። ግን እኔ ሜዳ ውስጥ ከገባሁ የምችለውን የአቅሜን ሁሉ አደርጋለሁ። ብዙ ጊዜ ቡና ከገባሁበት ወቅት ጀምሮ የተለያየ ቦታ ነው የምጫወተው። በለመድከት ቦታ አልነበረም እጫወት የነበረው። ይህ ተፅእኖ አድርጎብኝ ነበር። አሁን ቦታዎችን እየለመድኩኝ ጥሩ ለመንቀሳቀስ እየቻልኩ ነው።

” ታታሪነቱ የመጣው በፍላጎት ነው። እዛ ቦታ ላይ የተሰጠኝን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ካለኝ ፍላጎት የመጣ ነው ውጤታማ ያደረገኝ። ሌላ የተለየ ነገር የለውም።

” ዘንድሮ ከባለፉት ዓመታት የተሻለ አቋም እያሳየን ነው። ፈጣሪ ፈቅዶ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እናስባለን።”

በዛሬው ጨዋታ ሐት ትሪክ የሰራው አቡበከር ናስር አሥራት ቱንጆን በዚህ መልኩ ገልፆታል።

“ለእኔ ሁሉም አሪፍ ነበሩ። እንቅስቃሴያችን እንደ ቡድን ጥሩ ነበር። ግን ለእኔ ለየት ብሎ ያየሁት አሥራት ነበር። በጣም የሚገርም ብቃት አለው። ከኃላ ተነስቶ መጥቶ ጎል አስቆጥሯል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ያለቀላቸው ኳሶች ሲሰጥ ነበርና እሱን በደንብ ማመስገን እፈልጋለሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ