አዳማ እና ሰበታ የሚያደርጉትን ጨዋታ በዚህ መልኩ በዳሰሳችን ተመልክተነዋል።
በዕኩል ነጥቦች በወራጅ ቀጠናው ውስጥ የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች በጅማ የመጨረሻ ጨዋታቸው የሚጠብቋቸው ነጥቦች ለቀጣይ ተስፋቸው ወሳኝ ይሆናሉ።
አስረኛው ሳምንት እንደ አዳማ የደመቀለት አልነበረም። ባልተጠበቀ መልኩ ማሸነፉ ብቻ ሳይሆን ያሸነፈበት መንገድ የተጋጣሚውን የሀዋሳን ደካማ ጎን በአግባቡ በመጠቀም እና በጨዋታም በልጦ በመገኘት መሆኑ ውጤቱን ልዩ ያደርገዋል። አሁን ቡድኑ የሚኖርበት ፈተና ደግሞ ይህንን መልካም አቋም በምን መልኩ ማስቀጠል ይቻላል የሚለው ነው። አዳማ የነገ ተጋጣሚው ከሀዋሳ የበለጠ ለኳስ ቁጥጥር ትኩረት የሚሰጥ ከመሆኑ ባሻገር የኋላ መስመሩ ላይ ስህተት ሲሰራ የሚታይ በመሆኑ ተመሳሳይ የመልሶ ማጥቃት አካሄድን ሊከተል ይችላል። በተለይም የቡድኑ የቀኝ ወገን ላይ የበላይ አባይነህ እና ታፈሰ ሰርካ የሰመረ መናበብ ከተደገመ ለቡድኑ ያለው ጠቀሜታ የጎላ ይሆናል። ከቡድን እንቅስቃሴ ባለፈ እንደቴዎድሮስ ገብረእግዚያብሄር ያሉ ተጫዋቾች መልካም አቋምን ማሳየት አዳማ ይዞት ለሚገባው የጨዋታ ዕቅድ ተጨማሪ ጉልበት ይሆነዋል። አብዲሳ ጀማልም ሐት ትሪክ ከሰራበት ሳምንት በኃላ ግብ አምራችነቱ ይቀጥላል ወይ የሚለውን ከነገው ጨዋታ የምንጠብቅ ይሆናል።
ሰበታ ከተማ ሽንፈት በቀመሰባቸው የባህር ዳር እና የሲዳማ ጨዋታዎች የተሻለ ንቃት ታይቶበት በነበረው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ የመድረስ ብቃቱ በሆሳዕናው ጨዋታ ላይ ዳግም ተዳክሞ ተስተውሏል። በዋነኝነትም በአራት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረው የቡድኑ የፊት መስመር ድክመት ግን ትልቁ ስጋቱ ነው። የዚህ ችግር መንስኤ ዕድሎችን በብዛት ካለመፍጠርም የተገኙትንም በአግባቡ ከመጨረስም የመነጨ በመሆኑ ቡድኑ የሚወስደው የመፍትሄ እርምጃ ዘርፈ ብዙ እንዲሆን የሚያስገድድ ነው። በዚህ ረገድ በተደራራቢ ጉዳት ይበልጥ የሳሳው የቡድኑን የመሀል ክፍል ማስተካከል ከባድ የቤት ስራ ይመስላል። ሰበታ የነገ ተጋጣሚው የሚገኝበትን መነሳሳት በሚመጥን የቡድን መንፈስ ጨዋታውን መቅረብም ይጠበቅበታል። ያ ካልሆነ መነሳሳት የሚፈጥረው ታታሪነት የአዳማን የፊት መስመር እንቅስቃሴ ጉልበት ሊጨምረው የሰበታን የኃላ ክፍል የተለመዳ ከጫና የሚመነጭ ስህተት ደግሞ ሊያጎላው ይችላል። ያም ቢሆን ከውጤቱ አስፈላጊነት አንፃር የአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ቡድን የወትሮው የኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ ግን ደግሞ ፈጣን ያለ ጥቃት ላይ ተመስርቶ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል።
አዳማ ከተማ አምበሉ የኋላሸት ፍቃዱ እና ሱሌይማን መሀመድ ከጉዳት ያልተመለሱለት ሲሆን ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ ደግሞ ልምምድ ጀምሯል። በሌላ በኩል ወጌሻው ዮሐንስ ጌታቸው በሀዋሳው ጨዋታ ካርድ የተመዘዘበት በመሆኑ በቅጣት በዚህ ጨዋታ በኃላፊነቱ ላይ አይገኘም። በሰበታ ከተማ በኩልም መስዑድ መሀመድ ፣ ቢያድግልኝ ኤልያስ ፣ ፉዓድ ፈረጃ እና ታደለ መንገሻ ጉዳት ላይ የሚገኙ ሲሆን ያሬድ ሀሰን እና ዳንኤል ኃይሉም ቅጣት ላይ ናቸው።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– እስካሁን በተገናኙባቸው ስድስት ጨዋታዎች አዳማ ከተማ ሦስት ጊዜ በማሸነፍ የበላይነት አለው። ሰበታ ከተማ አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
– በስድስቱ ጨዋታዎች ስድስት ጎሎች ሲቆጠሩ አዳማ 4 ፣ ሰበታ 2 አስቆጥረዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
አዳማ ከተማ (4-3-3)
ታሪክ ጌትነት
ታፈሰ ሰርካ – ደስታ ጊቻሞ – ትዕግስቱ አበራ – አካሉ አበራ
ቴዎድሮስ ገ/እግዚያብሄር – ደሳለኝ ደባሽ – በቃሉ ገነነ
በላይ ዓባይነህ – አብዲሳ ጀማል – ፍሰሀ ቶማስ
ሰበታ ከተማ (4-3-3)
ምንተስኖት ዓሎ
ዓለምአየሁ ሙለታ – መሳይ ጻውሎስ – አንተነህ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ
ኢብራሂም ከድር – አብዱልባስጥ ከማል – አብዱልሀቪዝ ቶፊቅ
ፍፁም ገብረማርያም – እስራኤል እሸቱ – ቡልቻ ሹራ
© ሶከር ኢትዮጵያ