ሁለቱ አሰልጣኞች በጨዋታው ላይ ያላቸውን ሀሳብ ለሱፐር ስፖርት አካፍለዋል።
አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – ባህር ዳር ከተማ
ስለጨዋታው
በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ አደረጃጀት ነበረን። ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ባዬን አስገብተን የጨዋታ ሀሳባችንን ለመቀየር ሞክረናል። በጣም ወደ ኃላ ተስበው እየተከላከሉ ስለነበር በመልሶ ማጥቃት ያንን ተከላክለን በመስመር እና በቀዳዳ ለመግባት ነበር ሀሳባችን። ግን ከኋላ የሚላኩ አንዳንድ አላስፈላጊ ረጃጅም ኳሶች በቀላሉ እንዲከላከሉን አድርጓል።
በጨዋታ መሀል ለአህመድ ረሺድ ስላስተላለፉት መልዕክት
የመጀመሪያው ከኋላ ትልልቅ ክፍተቶች እየተውንላቸው ነበር። ያ ደግሞ በቀላሉ ጎል እንዲቆጠርብን አድርጓል። ሁልጊዜም ወደ ጎል በተጠጋን ቁጥር ጎሉን መሸፈን ይገባን ነበር። እኛ ግን ተጫዋቾቻችን እንደተዘረጉ በተከላካዮች መሀል የነበረው ክፍተት ጎል እንዲቆጠርብን አድርጓል። ያንን ነበር ለአህመድ ረሹድ እየነገርኩት የነበረው።
ብዙ ጎል ስለሚያስተናግደው የኋላ ክፍል
ችግሩን እንደቡድን ብመለከተው ይሻላል። ጥቃቅን የሚመስሉ ግን ዋጋ የሚያስከፍሉ ብዙ ስህተቶች ሜዳ ላይ እየታዩ ነው። እነዛን ማሻሻል ይጠበቅብናል። ተጫዋቾቹ የሚችሉትን እያደረጉ ነው። ቡድኑ ስህተቶች እየደጋገመ ከሆነ የእኔ ኃላፊነት ነው ያንን ማሻሻል። ተጨዋቾቼ ግን የሚችሉትን እያደረጉ እንደሆነ ይሰማኛል።
አሰልጣኝ የሱፍ ዓሊ – ጅማ አባ ጅፋር
ስለኋላ ክፍሉ ክፍተት
ተከላካይ ክፍል ላይ በተደጋጋሚ ሲጫወቱ የነበሩትን ልጆች በጉዳት እየቀያየርናቸው ነው የምናስገባቸው። ባሉን ሦስት ቀኖች ተከላካዮችን አንድ ላይ አሰርተን ነበር። ትንሽ ክፍተት ነበር። በጣም አስፍተን ነበር የምንጫወተው። ከዕረፍት በኋላ ያንን አስተካክለን እንድንገባ አድርገናል።
ከኋላ ስለተዉት ሰፊ ክፍተት
የእኛ የመስመር ተከላላዮች ተመላልሰው የመጫወት አቅም ያላቸው ናቸው። እነሱ ላይ ተገን አርገን ነው ከፍተን የተጫወትነው በመልሶ ማጥቃት ለመጠቀም ነበር። ሦስቱም ብዙም ለመከላከል አይመጡም ነበር። መሀል ላይ ይቆረጣሉ ፤ በእነሱ በሚጣለው ኳስ ለመጠቀም ነበር እንደዛ ስናደርግ የነበረው።
ስለቡድኑ መነሳሳት
ዛሬ ሁለቱም ከንቲባዎች መጥተው ብዙ ነገር ነው ቃል ሲገቡላቸው የነበረው ፤ በጎደለው ነገር እንዲሟላ እስከመልበሻ ቤት ድረስ መጥተው። ትልቅ ተነሳሽነት ነበራቸው። ውጤት ይዘን እንደምንወጣ ነበር ስንነጋገር የነበረውም። ያው አቻውን ይዘን ወጥተናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ