ከአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ጋር ከአንድ ቀን በፊት የተለያየው ሲዳማ ቡና በምትኩ አዲስ አሰልጣኝ ሾሟል፡፡
ከቀናት በፊት የሲዳማ ቡና ቦርድ ለአስራ አራት ዓመታት በሥራ አስኪያጅነት ሲያገልግሉ የነበሩት አቶ መንግሥቱ ሳሳሞ፣ ከ2010 አጋማሽ ጀምሮ በዋና አሰልጣኝነት ክለቡን ሲመሩ የነበሩት አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ እንዲሁም ረዳት አሰልጣኙ ያሬድ ገመቹ ማሰናበቱ የሚታወስ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ የረጅም ጊዜ ልምድ ያካበቱት ገብረመድኅን ኃይሌን በዋና አሰልጣኝነት እንዲመሩ መሾማቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች በአሰልጣኝነት ዘመናቸው በትራንስ፣ ባንኮች፣ መድን፣ መከላከያ፣ ደደቢት፣ ቡና፣ ጅማ አባ ቡና፣ ጅማ አባጅፋር እና መቐለ 70 እንደርታ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ማሰልጠን የቻሉ ሲሆን ጅማ አባጅፋር እና መቐለ 70 እንደርታን ለፕሪምየር ሊጉ ድል አብቅተዋል፡፡ ከመቐለ ጋር በያዝነው ዓመት ለሦስተኛ ዓመት ለመቆየት መስማማት ቢችሉም በሀገራችን በተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ ክለቡ መሳተፍ አለመቻሉን ተከትሎ አሰልጣኙም ያለፉትን ወራት ካለ ክለብ ከሰነበቱ በኃላ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ ተመልሰው በሲዳማ ቡና የምንመለከታቸው ይሆናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ