በቅርቡ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር በስምምነት የተለያዩት አሰልጣኝ ፍስሐ ጥዑመልሳን አሁን ስለ ወቅታዊ ጉዳዮች ይናገራሉ።
የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮው የውድድር ዘመን ከሚሰጡት አስተያየት ጋር ተያይዞ መነጋገሪያ ርዕስ የሆኑት አሰልጣኝ ፍስሐ ጥዑመልሳን ከተጫዋችነት ወደ አሰልጣኝነት ተሻግረው በታዳጊ ቡድን ጅማሮ ባደረገው የማሰልጠን ህይወታቸው የድሬዳዋ ሴቶች ቡድን አሰልጣኝ እና ከ2010 ጀምሮ የወንዶች ቡድን ምክትል አሰልጣኝ በመሆን ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን ባሳለፍነው የውድድር ዘመን አሰልጣኝ ስምኦን ዓባይን በመተካት ዋና አሰልጣኝ ሆነው እያገለገሉ መቆየታቸው ይታወቃል። በቅርቡ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር የተለያዩት አሰልጣኙ አሁን ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ይሄን ይናገራሉ።
የዘንድሮ የፕሪምየር ሊግ ቆይታቸው
ሊጉ በብዙ ክስተቶች የታጀበ ነው። ውድድሩ በዝግ መካሄዱ፣ ጨዋታዎቹ በዲኤስ ቲቪ የሚተላለፉ መሆናቸው እና በኮቪድ ምክንያት ከወራት በኃላ ተቋርጦ ከአስቸጋሪ ሁኔታ በኃላ መጀመሩ የተለየ ያደርገዋል። በአጠቃላይ ውድድሩ ጥሩ ነበር። አይረሴ ቆይታ አድርጌበታለው።
ከቡድኑ ጋር ስለነበራቸው ቆይታ
ጥሩ ቡድን ፈጣን እግርኳስ የሚጫወት አሰልቺ ያልነበረ ቶሎ ቶሎ ወደ ጎል የሚደርስ ቡድን ሰርቼያለው። ግን ችግሩ እኔ እድለኛ አይደለሁም። በተለይ ጅማ ላይ በነበረው ውድድር ዕድለኛ አልነበርንም። ምክንያቱም የግቡ ቋሚ የመለሷቸው ኳሶች ቢቆጠሩ ኖሮ አጥቂዎቻችን ኮከብ ይሆኑ ነበር። ሌሎች ቡድኖች ያላገኙትን ከጎል ጋር እየተገናኘን ያልተጠቀምንባቸው ብዙ ኳሶች የሚያስቆጩ ናቸው። ስለዚህ እድለኛ አለመሆን ነው። ብቻ ብዙ ሰርቼ ነበር ሰዎችን አምጥቼም የስነ ልቦናም ሥራ ሰርተን ነበር። ብዙ ለፍተን ጥረን ነበር እግርኳስ ጥሩ ቡድን ስለገነባህ ብቻ ሳይሆን ዕድል ያስፈልጋል። ሌላው ከያዝናቸው ስምንት ተከላካዮች ሰባቱ ጉዳት ላይ መሆናቸው ያሳደረብን ተፅዕኖ አለ።
ከቡድኑ ጋር ስለተለያዩበት ምክንያት
በመጀመርያ ቡድኑን በፍጥነት ወደ ውጤት እንዳመጣው ደብዳቤ ደረሰኝ። እኔም ከምክትሎቼ ጋር ተነጋግሬ ለቡድኑ ትክክለኛ ውጤት አመጣለው ብዬ መልስ በመስጠት ወደ ባህር ዳር ሄድኩኝ ባጋጣሚ ሥራ አስኪያጁ ደውሎ ክለቡ ሊያናግረኝ እንደሚፈልገኝ ጠራኝ ወደ ድሬደዋ ተመልሼ መጣሁ። ባጋጣሚ የክለቡ የቦርድ ኃላፊዎች የመንግሥት ስራ ስለነበረባቸው አላገኘሁም። አንድ ነገር መናገር የምፈገው የኔና የድሬዳዋ ጉዳይ የቤተሰብ ጉዳይ ነው። ወደ ድሬዳዋ ስመጣ አውቄዋለሁ፤ ማንም አሰልጣኝ ከውጤት መጥፋት ጋር ተያይዞ ሊነሳ ይችላል። እኔም ውጤት የለኝም። በዛ ነው የተነሳሁት። መነሳትም ነበረብኝ። ከአመራሮቹ ጋር ብገናኝም ባልገናኝም በሰላም የሚያልቅ የቤተሰብ ጉዳይ ነው።
ከክለቡ ጋር በመለያየታቸው ስለተሰማቸው ስሜት
ምንም የተሰማኝ ነገር የለም። ትንሽ አሪፍ ቡድን ሰርቼ ውጤታማ ሆኜ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ከምታወቅበት በላይ የተሻለ መታወቅ ቢኖረኝ ደስ ይለኛል። ቡድኑ ሒደቱን ነው የጠበቀው። ምንም የተሰማኝ ነገር የለም። ምክንያቱም በቀጣይ የሚጠብቁኝ የተሻሉ ሥራዎች አሉ።
ስለ አዲሱ አሰልጣኝ
በጣም ጓደኛዬ ነው። ብዙ ውለታ የዋለልኝ ነው። ድሬደዋ ሲመጣ እርሱን በክብር ለመቀበል ቸኩያለው። ሞሮኮ በተካሄደው የአሰልጣኞች ስልጠና ላይ ብዙ ነገሮችን ያደረገልኝ እጅግ መልካም ሰው ነው። ከዚህ በላይ ትልቅ አሰልጣኝ ነው። አንዳንዴ ያላልኩት ነገር በሚዲያ ሲባል ቅር ብሎኛል። እኔ ለየትኛውም ሚዲያ አስተያየት አልሰጠሁም። ዘማርያም በጣም የማከብረው ሰው ነው።
በቀጣይ ወደ ስልጠናው ስለመመለስ
መጀመርያ ጅማ ሆኜ ወገቤን አሞኛል ብዬ
ነበር። በኃላ ወደ ድሬደዋ መጥቼ ስመረመር ኩላሊት መሆኑን ተነግሮኛል። ስለዚህ በቂ እረፍት ማድረግ አለብኝ። ሁሉም ነገር የሚሆነው ጤና ሲሆን ነው።
በመጨረሻ
እግርኳስን ሳሰለጥን ወደ ሃያ አምስት ዓመት ሆኖኛል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ያው በድሬደዋ ብዙ ክለቦች የለውም ያም ቢሆን በፕሮጀክት በመላው ኢትዮጵያ ውድድሮች ቡድን ይዤ ብዙ ስራ ሰርቻለሁ። በፕሪምየር ሊጉ አራተኛ ዓመቴ ነው፤ ብዙ ልምድ የለኝም። በአራት ዓመት ውስጥ ክለቡ እኔን አምኖኝ ከማንም ጋር ሳያወዳድረኝ አምኖኝ ነው የሰጠኝ። በዚህም የክለቡን ቦርድ አመሰግናለሁ። ከክለቡ ብነሳም ድሬዳዋ አሁንም ክለቤ ነው። የድሬደዋ ልጅ ነኝ በሚዲያ የሚወራውን እንተወው። በአሰልጣኝነቱ ባይሆን እንኳን ቡድኑን በሀሳብ እረዳለሁ። ወደ ሌላ ክለብ ሄጄ የምሠራበት ዕድል ከፍቶልኛል። ሁሉንም አካላት በጣም አመግናለሁ። በነገራችን ላይ ዲኤስ ቲቪዎች እየደወሉልኝ ነው። ውበታችንን እያጣን ነው፤ ድሬዳዋ እንገናኛለን እያሉኝ ነው። እኔም በናፍቆት እጠብቃቸዋለው። (እየሳቁ)
© ሶከር ኢትዮጵያ