የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 0-0 ሀዲያ ሆሳዕና

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስራ ሁለተኛ ሳምንት የረፋድ ጨዋታ ቡና እና ሆሳዕና ያል ጎል አቻ ከተለያዩ በኋላ ተከታዩን አስተያየት ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለ ውጤቱ

ከውጤት አንፃር የምንፈልገውን አላገኘንም። ጨዋታውን ከመቆጣጠር አንፃር ግን ተቆጣጥረናል። ጨዋታ መቆጣጠር ብዙ ነገር ነው። የጎል እድሎችን የመፍጠር አጋጣሚ የምታገኝበት ነው። በተለይ ከእረፍት በኋላ አስራ አንዱም በራሳቸው የሜዳ አጋማሽ ነበሩ። ስለዚህ የመጫወቻ ሜዳዎች የጠበቡ ናቸው። በዛ ውስጥ ያለ የቅብብል ስኬት፣ የአዕምሮ ግንኙነት የመሳሰለው ነገር መዳበር አለበት። አንድ የምናስበው የተከፈቱ ቦታዎች አሉ። እሱን ግን በተገቢው መንገድ አልሰራንበትም። በአጠቃላይ ጨዋታውን ከመቆጣጠራችን አንፃር የምንፈልገውን ውጤት አግኝተናል ማለት አይቻልም።

ስለ ተሞከሩባቸው ኳሶች

የመጀመርያው ያገኙት እድል የኛ አንድ ተጫዋች ሊዘጋጅበት የሚገባ ነበር። ከግብ ጠባቂው ጋር የሚኖረው ግንኙነት አለ። ሆኖም የተዘናጋ መሰለኝ እኔን አይጠቀምም በሚል። በዚህም እኩል እድል የነበረው ኳስ ስለነበር እነሱ አገኙት። ተከላካዩ ከአቤል ጋር ለመገናኘት ዝግጁ ቢሆን ኖሮ እነሱ ያንን ኳስ ማግኘት አይችሉም ነበር።

ስለ ቀጣይ ጨዋታዎች

እኛ ሁልጊዜ የጨዋታ የበላይነት መውሰድ እንፈልጋለን። በዛ ውስጥ ውጤት ይገኛል ብለን ስለምናምን። ከዚህ ጋር ተያይዞ ሁሉንም ጨዋታ በአሸናፊነት መወጣት ነው የምንፈልገው። ዛሬ አቻ ወጥተናል፤ በቀጣይ ጨዋታዎች እያሸነፍን መጓዝ ነው የምንፈልገው።

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና

ስለ ውጤቱ

ማሸነፍ እንደነበረብን አምናለሁ። ቡናም ቢያሸንፍ ወይም ብንሸናነፍ ለውድድሩ ድምቀት ይሆን ነበር። ካገኘቸው የጎል አጋጣሚዎች አንፃር አቻ መውጣታችን ግን ብዙም አልተመቸኝም። ዞሮ ዞሮ ቡናዎች ይዘውት የቀረቡት የአጨዋወት ስልት እኛ አቅደን ለገባነው ሥራ አግዞናል ብዬ አስባለሁ።

ስለ ሁለተኛ አጋማሽ ማፈግፈግ

እንዲህ ለማድረግ የፈለግነው ያለንን አቅም በማገናዘብ ነው። የመጫወት አቅማቸው፣ ከኳስ ጋር ያላቸው ቁርኝት ስታስብ የምታጣቸው ነገሮች ብዙ ናቸው። ቡናዎች ደግሞ ኳስ ካገኙ የመቀነስ አቅም አላቸው። ያንን የመጫወቻ ቦታ ማሳጣት ደግሞ ሌላው የኛ የታክቲክ አቀራረብ ነው። ስለዚህ ባቀድነው መሰረት ነው እነሱ የሄዱልን። እኛም ያሰብነውን ተግብረናል፤ የአጨራረስ ችግር ነው እንጂ። ወሳኝ የምንላቸው በጉዳት ያልገቡ ተጫዋቾች ቡድኔን ክፉኛ አሳስተውታል። በሚቀጥለው ተሟልተን ለመምጣት እንሞክራለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ