ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ12ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በ12ኛው ሳምንት ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጥሩ የተንቀሳቀሱ ተጫዋቾችን እንደሚከተለው መርጠናል።

አሰላለፍ : 4-3-3
ግብ ጠባቂ

አቡበከር ኑሪ – ጅማ አባጅፋር

ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ ሁለተኛ ተከታታይ ጨዋታውን ያከናወነው ወጣቱ የግብ ዘብ አቡበከር በአዲሱ የቡድኑ አሠልጣኝ የመጀመሪያ ጨዋታ ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል። በጥሩ ቅፅበታዊ ቅልጥፍናዎች የሲዳማ ቡናዎችን የግብ ሙከራ ሲያመከን የነበረው አቡበከር ቡድኑ ግብ ሳያስተናግድ የዓመቱን የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ ይዞ እንዲወጣ ያደረገው ጥረት የሚያስመሰግነው ነበር። በዚህም በጨዋታው የተሞከሩበት 7 ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን በማዳን ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል።

ተከላካዮች

ላውረንስ ላርቴ – ሀዋሳ ከተማ

ጋናዊው የመሐል ተከላካይ ላውረንስ ላርቴ በ12ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር ባሳየው ድንቅ ብቃት ለሦስተኛ ጊዜ የሳምንቱ ምርጥ ቡድናችን ውስጥ መካተት ችሏል። ቁመተ መለሎው ተከላካይ ቡድኑ በሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ 2-1 ቢሸነፍም በግሉ ያሳለፈው ጊዜ መልካም ነበር። ከምንም በላይ ከአጣማሪው ምኞት ደበበ ጋር በመሆን የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሙጂብ ቃሲም ከጨዋታው ውጪ ያደረገበት እና በሁለተኛው አጋማሽ ቡድኑ አብዝቶ ሲያጠቃ ከኋላ የነበረውን ክፍተት የሸፈነበት መንገድ ላይ ተንተርሰን በሳምንቱ የተሻለ ተጨዋች ባልታየበት የቀኝ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ አካተነዋል።

መላኩ ወልዴ – ጅማ አባ ጅፋር

ጅማ አባ ጅፋር በሊጉ ያከናወናቸው ሁሉም ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ መጫወት የቻለው መላኩ በሲዳማው ጨዋታ ያሳየው ብቃት ድንቅ ነበር። በተለይ ተጫዋቹ መከላከልን ምርጫው አድርጎ ወደ ሜዳ የገባውን ቡድን ከኋላ ሆኖ ሲመራ እና ሲያደራጅ የነበረበት መንገድ መልካም ነበር። ከምንም በላይ ደግሞ ከፊት ለፊቱ የነበሩትን ፈጣኖቹን የሲዳማ አጥቂዎች ለመቆጣጠር የሞከረበት እና ከመስመር ወደ ሳጥን ሲሻገሩ የነበሩትን ኳሶች ሲያፀዳ ድንቅ ነበር።

መሳይ ጻውሎስ – ሰበታ ከተማ

ሰበታ ከተማ ሁለተኛ ተከታታይ ድሉን አንድም ግብ ሳያስተናግድ እንዲወጣ ካስቻሉ ተጫዋቾች መካከል አንደኛው መሳይ ጻውሎስ ነው። የመሐል ተከላካዩ ቡድኑ ወልቂጤን ሲገጥም የተሰነዘሩበትን ጥቃቶች በማክሸፍ እና በመመከት ጊዜውን አሳልፏል። በተለይም ከመከላከል ወደ ማጥቃት በፈጣን ሽግግሮች የሰበታ የግብ ክልል ሲደርሱ የነበሩ የወልቂጤ ተጫዋቾችን የተቆጣጠረበት ብቃት መልካም ነበር። በተጨማሪም ቡድኑ የቆሙ ኳሶችን በሚያገኝበት ሰዓት አጋጣሚዎቹን ወደ ግብነት ለመቀየር ሲጥር ነበር። ብቸኛዋ የአሸናፊነት ጎልንም ፍፁም ሲያስቆጥር ተጫዋቹ በግንባሩ ሞክሮት በግቡ ብረት የተመለሰው ኳስ መነሻ ነበር።

አምሳሉ ጥላሁን – ፋሲል ከነማ

ፋሲል ከነማዎች የሊጉን መሪነት አጥብቀው የያዙበትን ድል ትላንት ሲያገኙ የማሸነፊያውን ጎል በአስደናቂ ሁኔታ ከመረብ ያሳረፈው አምሳሉ ጥላሁን በምርጥ ቡድናችን የግራ መስመር ተከላካይነት ቦታን አግኝቷል። ለማጥቃት ባለው ፍላጎት የተጋጣሚ የግብ ክልል አካባቢ የማይጠፋው አምሳሉ የቡድኑን የግራ መስመር የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲዘውር ታይቷል። ከምንም በላይ ተጫዋቹ ፈጣን የመስመር ላይ ሩጫዎችን በማድረግ የሀዋሳዎችን የመከላከል ትኩረት ይዞ ተጫውቷል። በተጨማሪም ዋነኛ ኃላፊነቱ የሆነውን የመከላከል እንቅስቃሴ በሚገባ በመተግበር ቡድኑ በእርሱ በኩል እንዳይጠቃ አስተዋጽኦ አድርጓል።

አማካዮች

በረከት ወልዴ – ወላይታ ዲቻ

በተከላካይ አማካይ ስፍራ የሚጫወተው በረከት ቡድኑ ባህር ዳርን ገጥሞ አንድ ነጥብ ይዞ ሲወጣ የነበረው ሚና ትንሽ አልነበረም። በተለይም ተጫዋቹ የተጋጣሚ ቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች የነበረውን ፍፁም ዓለሙን እንቅስቃሴ ተቆጣጥሮ ባህር ዳሮች መሐል ለመሐል ጥቃት እንዳይሰነዝሩ ያደረገበት እና የተከላካይ ክፍሉ እንዳይጋለጥ የታተረበት ብቃት እጅግ አድናቆትን የሚያስቸረው ነበር። እርግጥ ተጫዋቹ በሁለተኛ የቢጫ ካርድ ከሜዳ ቢወጣም ለቀይ የዳረገው ፍፁም ላይ የሰራው ይየሳጥን ውስጥ ጥፋት ቡድኑን ግብ እንዳይቆጠርበት ያደረገ ነበር። የቡድን ጓደኛው መክብብ ፍፁም ቅጣት ምቱን በማዳኑም የበረከት ውሳኔ ውጤት አስገኝቶለታል።

አቤል እንዳለ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

የቀደሞው የደደቢት ኮከብ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተፅዕኔው ወርዶ ቢታይም በቅርብ ጨዋታዎች ቡድኑ የጎደለውን ነገር ከእርሱ ማግኘት እንደሚችል እያሳየ ይገኛል። የአዳማውን ጨዋታ በመጀመሪያ አሰላለፍ መጀመር የቻለው አቤል በጊዮርጊስ የማጥቃት ሂደት ውስጥ ከአጥቂዎች ጀርባ ባለው ቦታ ላይ ያለውን ክፍተት ለመድፈን ያረገው ጥረት አመርቂ ነበር። ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በቀረበው እንቅስቃሴው መነሻነትም የጨራሽ አጥቂነት ባህሪን በተላበሰ መልኩ ግሩም ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

አልሀሰን ካሉሻ – ሀዲያ ሆሳዕና

አሀን አሁን የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ በተደጋጋሚ እየታየ የሚገኘው ካለሻ አልሀሰን በቡናው ጨዋታ በግሉ ጥሩ ተንቀሳቅሷል። አብዛኛው የቡድኑ ተሰላፊዎች በመከላከል ላይ ያተኮረውን የ የዋታ ዕቅድ በመተግበር ላይ ያተኮሩ ሲሆን የዚሁ አጨዋወት አካል የነበረው ካሉሻ ሀዲያ ሆሳዕና ከኳስ ጋር ሲሆን ስስ የነበረውን የፊት መስመር ለማግኘት ቀድሞ ይገኝ ነበር። ከየጋጣሚ የቅብብል ስህተቶች የተገኙትን እና ከመልሶ ማጥቃት መነሻነት የተነሱት አብዛኞቹ የቡድኑ ሙከራዎች ላይም ጋናዊው አማካይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ሲያደርግ ተመልክተነዋል።

አጥቂዎች

ሽመክት ጉግሳ – ፋሲል ከነማ

ታታሪ እና አይደክሜው የመስመር ተጫዋች ሽመክት ጉግሳ ቡድኑ ሀዋሳን ሲረታ ያሳየው ብቃት ምርጥ ቡድናችን ውስጥ በመስመር አጥቂነት እንዲካተት አስችሎታል። ለቡድኑ ያለውን በመስጠት የማይታማው ሽመክት በትላንትናው ጨዋታ በረከት ያስቆጠረውን ግብ አመቻችቶ ከማቀበሉ በተጨማሪ በግሉ የሚያደርጋቸው የመስመር ላይ እንቅስቃሴዎች ጥሩ ነበሩ። በተጨማሪም የጨዋታው የኃይል ሚዛን ወደ ሀዋሳዎች ባጋደለበት ሰዓትም ቡድኑ እንዳይጠቃ ወደ ኋላ እየተመለሰ እንዲሁም ወደ መሀል እያጠበበ በመግባት ተገቢውን ሽፋን ሲሰጥ ተስተውሏል።

አማኑኤል ገብረሚካኤል – ቅዱስ ጊዮርጊስ

12ኛው ሳምንት ልዩ ሆኖ ካለፈላቸው ተጨዋቾች መሀል እንደ ቀድሞው የመቐለ 70 እንደርታ አማኑኤል ገብረሚካኤል ቀኑ የደመቀለት ያለ አይመስልም። አዲሱን ክለቡን ከተቀላቀለ በኋላ ከአሰላለፍም ጠፍቶ የነበረው ተጨዋቹ ወደ ሜዳ የመግባት ዕድል ባገኘባቸው ጨዋታዎችም እምብዛም ውጤታማ ሳይሆን ቆይቷል። በዚህኛው ሳምንት ግን ቡድኑ አዳማ ላይ አራት ግቦችን ሲያስቆጥር ሁለቱን በስሙ አስመዝግቦ ለአንደኛው ግብ መገኘት ደግሞ ምክንያት መሆን ችሏል። በሙሉ የጨዋታው ጊዜም እርሱ በተሰለፈበት መስመር የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ አስፈሪ ሆኖ እንዲቀጥል አድርጓል።

ጌታነህ ከበደ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

የቅዱስ ጊዮርጊሱ አንበል ከአራት ሳምንታት ቆይታ በኋላ ዳግም ግብ ወደ ማስቆጠሩ የተመለሰበትን ጨዋታ አሳልፏል። አሁንም ከፍ ባለ የራስ መተማመን ላይ የሚገኝ መሆኑን ባስመሰከረበት የአዳማው ጨዋታ እንደተለመደው የቡድን ጓደኞቹን ይመራ የነበረበት መንገድም የአንበልነት ኃላፊነቱን በመወጣቱ እንደማይታማ ያሳየ ነበር። ጌታነህ ከአራቱ ግቤች አንዱን ማስቆጠሩ ብቻ ሳይሆን ከቀሩት ውስጥ ሁለቱ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ በማድረግ ለቡድኑ ውጤት ማማር ዓይነተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል።

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ጀማ አባጅፋር

አዲሱን እና ከባዱን ኃላፊነት በድል የጀመሩት አሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ቡድናቸው የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል እንዲያገኝ አስችለዋል። ከምንም በላይ ደግሞ በሊጉ ከፍተኛ የሆነውን በ10 የጨዋታ ሳምንታት 23 ጎሎች ያስተናገደውን ቡድን በቶሎ በማጠናከር ከሁለተኛ ሳምንት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ግብ ሳያስተናግድ እንዲወጣ ማስቻላቸው የሳምንቱ ኮከብነትን እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።

ተጠባባቂዎች

መክብብ ደገፉ – ወላይታ ድቻ
ኤልያስ አታሮ – ጅማ አባ ጅፋር
ይበልጣል ሽባባው – ወልቂጤ ከተማ
ሀብታሙ ተከስተ – ፋሲል ከነማ
አማኑኤል ጎበና – ሀዲያ ሆሳዕና
በረከት ደስታ – ፋሲል ከነማ
ፍፁም ገብረማርያም – ሰበታ ከተማ


© ሶከር ኢትዮጵያ