ቅድመ ዳሰሳ | ሀዲያ ሆሳዕና ከ ጅማ አባ ጅፋር

ነገ ረፋድ ላይ በሚከናወነው ጨዋታ ዙሪያ ተከታዩን ዳሰሳ አዘጋጅተናል።

በሰንጠረዡ አናት እና ግርጌ ላይ ላሉባቸው ፉክክሮች ከነገው ጨዋታ ውጤት የሚጠብቁት ሀዲያ ሆሳዕና እና ጅማ አባ ጅፋር የዕለቱን የመጀመሪያ ፍልሚያ ያደርጋሉ። የዛሬዎቹን ውጤቶች ተከትሎ ከበላዩ ያሉት ቡና እና ጊዮርጊስ በአራት ነጥቦች የራቁት ሀዲያ ሆሳዕና የቻምፒዮንነት ፉክክር ውስጥ ለመቆየት ሙሉ ነጥብ ማሳካት ይኖርበታል። በሌላ ጎን ከበስተኋላው ያለው አዳማ በመሸነፉ ባለበት የረጋው ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ አሁንም አንድ ደረጃን የማሻሻል ተስፋን ይዞ ወደ ሜዳ ይገባል።

12ኛው ሳምንት ላይ በተደረጉ ጨዋታዎች ሁለቱ ቡድኖች የተለያዩ ውጤቶች ያስመዝግቡ እንጂ የሜዳ ላይ አቀራረባቸው ተመሳሳይ ነበር። ሀዲያ ሆሳዕና ኢትዮጵያ ቡናን እንቅስቃሴ በሚገባ በመቆጣጠር ነጥብ ሲጋራ ጅማ በበኩሉ የሲዳማን ጥቃት ተቋቁሞ ውጤቱን በማስጠበቅ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ ነጥብ ማሳካት ችሎ ነበር። የነገው የቡድኖቹ ጨዋታ ግን ከእነዚህ ጨዋታዎች የተሻለ ወደ ፊት የመሄድ እና የማጥቃት ፍላጎት የሚንፀባረቅበት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

ሁለቱ አሰልጣኞች ማጥቃትን ምርጫቸው ቢያደርጉም ግን የየራሳቸው ፈተና ያለባቸው መሆኑ መዘንጋት የለበትም። አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ባለፉት አራት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደው ቡድናቸውን ለጥንቃቄ ያመዘነ አቀራረብ ለቀቅ አድርገው እንደሚገቡ ቢታሰብም ተደጋጋሚ ድሎችን ያስገኘላቸው የፊት መስመራቸው የሦስትዮሽ ጥምረት አሁንም አለመሟላቱ እንቅፋት ሊሆንባቸው ይችላል። ቡድናቸውን በፉክክር ጨዋታ የመመዘን ዕድሉን ያገኙት አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያምም የመከላከሉን ያህል በማጥቃቱ ረገድ የተደራጀ አቀራረብን ይዞ ለመምጣት ጊዜ እንቅፋት ሊሆንባቸው ይችላል።

በጥቅሉ ሲታይ ግን ጅማ አባ ጅፋር ለኳስ ቁጥጥር የሚያመዝን አጨዋወትን ምርጫው ሊያደርግ እንደሚችል ይታሰባል። ነገር ግን ከቡድኑ ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ከፊት አጥቂዎቹ እና የማጥቃት ባህሪ ካላቸው አማካዮቹ ውጪ ቀሪዎቹን ተጨዋቾችን በማጥቃት ላይ ለማሳተፍ ላይደፍር መቻሉ የሀዲያን ጠንካራ መከላከል ማለፍ እንዳይከብደው ያሰጋል። በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ከግብ ማስቆጠሩ ርቆ መቆየቱ የሚገኙ ዕድሎችን በአግባቡ መጨረስ ላይ ክፍተት እንዲኖርበት ሊያደርግ ይችላል። ከዚህ ውጪ ከመስመር ተከላካዮችቹ የሚነሱ ኳሶች እና በፈጣን ሽግግር ጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው ካሉሻ አልሀሰንን ቀማሪነት በሚጠይቁ ጥቃቶች ጅማ ደጃፍ ሊደርስ ይችላል።

ጅማ አባ ጅፋር ሀብታሙ ንጉሴን አሁንም በጉዳት ሲያጣ ቤካም አብደላ የሚመለስለት ሲሆን የብዙአየሁ እንዳሻው መሰለፍ ግን አለየለትም። ሀዲያ ሆሳዕና የአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት ያለበት ሱሌይማን ሀሚድን ጨምሮ ሳሊፉ ፎፋና እና ቴዎድሮስ በቀለን ግልጋሎት የማያገኝ ሲሆን ዳዋ ሆቴሳ ፣ መድሀኔ ብርሀኔ እና ተስፋዬ አለባቸው ደግሞ ወደ ሜዳ እንደሚመለሱለት ይጠበቃል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– 2008 ላይ በሊጉ የተሳተፈው ሆዲያ ሆሳዕና እና ከ2010 ጀምሮ በውድድሩ ላይ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር ጋር ነገ ለመጀመሪያ ጊዜ ይገናኛሉ። በተሰረዘው የውድድር ዓመት ግን ሀዲያ ሆሳዕና 1-0 ማሸነፍ ችሎ ነበር።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዲያ ሆሳዕና (4-3-3)

መሐመድ ሙንታሪ

መድሀኔ ብርሀኔ – ኢሴንዴ አይዛክ – ተስፋዬ በቀለ – ሄኖክ አርፌጮ

ካሉሻ አልሀሰን – ተስፋዬ አለባቸው – አማኑኤል ጎበና

ቢስማርክ አፒያ – ዳዋ ሆቴሳ – ዱላ ሙላቱ

ጅማ አባ ጅፋር (4-2-3-1)

ጃኮ ፔንዜ

ወንድምአገኝ ማርቆስ – መላኩ ወልዴ – ውብሸት ዓለማየሁ – ኤልያስ አታሮ

አብርሀም ታምራት – ንጋቱ ገብረስላሴ

ተመስገን ደረሰ – ሙሉቀን ታሪኩ – ሱራፌል ዐወል

ሳዲቅ ሴቾ


© ሶከር ኢትዮጵያ