ሪፖርት | የአልሀሰን ካሉሻ የጭማሪ ደቂቃ ጎል ነብሮቹን ለድል አብቅቷል

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን የረፋድ ጨዋታ ሆሳዕና እና አባጅፋር ያደረጉት ጨዋታ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረ ጎል በሆራዕና አሸናፊነት ተጠናቋል።

በጉዳት፣ ቅጣት እና ኮንትራት ጉዳዮች ስብስባቸው የሳሳው አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከቡና አቻ ከተለያየው ስብስብ አምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት ላይ የሚገኘው ሱሌይማን ሀሚድን በፀጋሰው ደማሙ ሚካኤል ጆርጅን ከጉዳት በተመለሳው ዳዋ ሆቴሳ ምትክ ለጨዋታው ቀርበዋል። አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በበኩላቸው ባለፈው ሳምንት የዓመቱ የመጀመርያ ሦስት ነጥብ ያስገኘው ቡድናቸው ላይ ምንም ለውጥ ሳያደርጉበት ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ሀዲያ ሆሳዕና ብልጫ በጉልህ በታየበት የመጀመርያ አጋማሽ ነብሮቹ በዚህ ዓመት ካደረጓቸው ጨዋታዎች በተሻለ በርካታ የጎል ዕድሎችን መፍጠር ቢችሉም ሙከራዎቻቸው ኢላማቸውን የሳቱ ነበሩ። በአስረኛው ደቂቃ ቢስማርክ ከግማሽ ጨረቃ መትቶ ቋሚ ገጭቶ በተመለሰበት ኳስ ወደ ጎል መቅረብ የጀመሩት ነብሮቹ በ21ኛው ደቂቃ ወንድማገኝ በቢስማርክ ላይ በሰራው ጥፋት የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው የነበረ ቢሆንም ረዳት ዳኛው ቀድመው የጨዋታ ውጪ በማለታቸው ሳይሰጥ ቀርቷል። ከክስተቱ ሁለት ደቂቃ በኋላም ዱላ ሙላተለ በጥሩ ሁኔታ የጣለለትን ኳስ ዱላ ሙላቱ ከቀኝ መስመር አመቻችቶለት አማኑኤል ወደ ጎል መትቶ አግዳሚውን የመለሰበትም ሌላው ጠንካራ ሙከራ ነበር።

ወደ አባ ጅፋር የግብ ክልል ተጠግተው ጎል ለማግኘት ጥረታቸውን የቀጠሉት ሆሳዕናዎች በቀሪዎቹ የመጀመርያዎቹ አጋማሽ ደቂቃዎች ጥብቅ የነበረው የተጋጣሚያቸው የመከላከል አደረጃጀትን ለማስከፈት ተቸግረው የነበረ በመሆኑ ከርቀት ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተውለዋል። በዚህም ዱላ እና አዲስ ከርቀት ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ አድርገዋል።

በመጀመርያው አጋማሽ ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ የማጥቃት አጋጣሚዎች መፍጠር ያልቻሉት ጅማዎች በ45ኛው ደቂቃ ተመስገን ደረሰ ከርቀት መትቶ ሙንታሪ ካወጣበት ውጪ ሙከራ ሳያደርጉ ወደ እረፍት አምርተዋል።

በተመሳሳይ እንቅስቃሴ ነገር ግን በጅማ አባጅፋሮች አስቆጪ ሙከራዎች በታጀበው ሁለተኛው አጋማሽ ጅማዎች የጠሩ እድሎችን በመፍጠር የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም ሳይጠቀሙባቸዎ ቀርዋል። በ49ኛው ደቂቃ ከሱራፌል የተላከለትን ኳስ ሳዲቅ ሴቾ ከግብ ጠባቂው አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ወደውጪ የወጣበት ሙከራ እንዲሁም በሁለት አጋጣሚዎች ከተከላካዮች ቀምተው ባደረጉት ጥቃት ሱራፌል ዐወል ከጎሉ ፊት ለፊት ግልፅ አጋጣሚ አግኝቶ ወደ ውጪ የሰደደው ኳስ ጅማን ለጎል ያቃረቡ ነበሩ።

በሁለተኛው አጋማሽ ዱላ ሙላቱ ወደ መስመር ተከላካይነት ከተሸጋገረ ፍጥነቱን በመጠቀም በሚያሻግራቸው ኳሶች እድሎች የፈጠሩት ሆሳዕናዎች ጠንካራ የሚባሉ ባይሆኑም በአልሀሰን እና ዳዋ ሆቴሳ አማካኝነት ሙከራዎች አድርገዋል።

ጎል ሳይቆጠርበት ሊጠናቀቅ ተቃርቦ የነበረውን ጨዋታ በመጨረሻም ጋናዊው አማካይ አልሀሰን ካሉሻ ነፍስ ዘርቶበታል። በጭማሪው አራተኛ ደቂቃ ዱላ ሙላቱ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ በተቃራኒ አቅጣጫ ነፃ የነበረው ቢስማርክ አግኝቶ ተጫዋቹ ወደ መሐል በግንባሩ ገጭቶ የላከውን ኳስ ጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው አልሀሰን በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ለሆሳዕና ጣፋጭ ሦስት ነጥብ አስገኝቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ