ቅድመ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

የሳምንቱ ተጠባቂ መርሐ-ግብር የሆነውን የዐፄዎቹን እና የፈረሰኖቹን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ከተከታታይ ስድስት የድል ጨዋታዎች በኋላ በ12ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር ነጥብ የጣሉት ፋሲል ከነማዎች ዳግም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ እና የሊጉ መሪነታቸውን ለማጠናከር ነገን ይጠባበቃሉ። ወልቂጤ ከተማን 4-3 አሸንፈው ለዚህኛው ወሳኝ ጨዋታ የቀረቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በበኩላቸው ያገኙትን የአሸናፊነት መንገድ ለማስቀጠል እና ከመሪው ፋሲል ከነማ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት የማሳነስ ዓላማን ሰንቀው ወደ ሜዳ ይገባሉ።

ትክክለኛ የዋንጫ ተፎካካሪ ቡድን የሚመስለው ፋሲል ከነማ ከአስደናቂው የስድስት ጨዋታዎች የድል ጉዞ በኋላ በሰበታ ከተማ ነጥበ ሲጥል ያሳየው ብቃት ብዙ የሚያስተቸው ነበር። በተለይ ቡድኑ እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ጨዋታዎች ኳስን በሚገባ አለመቆጣጠሩ፣ ስል ሙከራዎችን ለመሰንዘር መቦዘኑ እና ጥቃቶችን በሚገባ መመከት አለመቻሉ በጉልህ ታይቷል። ከምንም በላይ ደግሞ ቡድኑ ጨዋታውን ለመቆጣጠር የሄደበት ርቀት እምብዛም መሆኑ በዕለቱ የቡድኑ ድክመት ሆኖ አልፏል። በተጨማሪም ግቡን ሳያስደፍር ለአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ዘልቆ የነበረው የቡድኑ የተከላካይ መስመር ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ግብ ማስተናገድ ጀምሯል። እርግጥ በሁለቱ ጨዋታዎች ያስተናገዳቸው ግቦች ከሁለት የዘለሉ ባይሆኑም ቡድኑ እውነተኛ የዋንጫ ተፎካካሪ ለመሆን ወደ ጠንካራ የኋላ መስመሩ መመለስ ያስፈልገዋል።

የሊጉ የአንደኛ ዙር መባቻ ላይ በሙጂብ ቃሲም ጎሎች ተንጠልጥሎ የነበረው ቡድኑ አሁን ላይ ሌሎች ግብ ማስቆጠሪያ አማራጮችን እያገኘ ይመስላል። በዚህም የመስመር አጥቂዎቹ በረከት እና ሽመክት ለቡድኑ ግብ እያስቆጠሩ መተዋል። በተጨማሪም ስድስት የአማካይ መስመር ተጫዋቾች ለቡድኑ ቢያንስ አንድ ግብ አስቆጥረዋል። ከዚህ መነሻነት ቡድኑ የግብ ማስቆጠሪያ አማራጭ እያገኘ መጥቷል። ከምንም በላይ ግን በነገው ጨዋታ የሁለቱ ፈጣን የመስመር ላይ አጥቂዎች (ሽመክት እና በረከት) ፍጥነት የታከለበት እንቅስቃሴ ለቡድኑ የግብ ማግኛ ሁነኛ አማራጭ ሊሆን ይችላል።

ዐፄዎቹ በጉዳት አልያም በቅጣት በነገው ጨዋታ የሚያጡት ተጫዋች አይኖርም። ጉዳት ላይ የነበረው ሰዒድ ልምምድ መጀመሩ ተሰምቷል። በአምስት ቢጫ ምክንያት ቡድኑ ከሰበታ ጋር አቻ ሲለያይ ወደ ሜዳ ገብቶ ያልነበረው አምሳሉም ቅጣቱን ጨርሶ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሆኗል።

ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ተጋጣሚ ላይ ስምንት ጎሎችን በማስቆጠር የቀድሞ አስፈሪነቱን ያገኘ የሚመስለው ቅዱስ ጊዮርጊስ በነገው ጨዋታ ቀላል የማይባል ፈተና እንደሚጠብቀው ይታመናል። በመጀመሪያው ዙር የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ካደረጋቸው 13 ጨዋታዎች በሦስቱ ብቻ ግቡን ሳያስደፍር የወጣው ቡድኑ የኋላ መስመሩ አስተማማኝ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ታይቷል። በመጨረሻዎቹ እና አራት አራት ጎሎችን ባስቆጠረባቸው ያለፉት ሁለት ጨዋታዎች እንኳን ቡድኑ አምስት ግቦችን አስተናግዷል። ከዚህ መነሻነት የቡድኑ አጠቃላይ የመከላከል መዋቅር ችግር ለሊጉ መሪ ፋሲል ከነማዎች በጎ ነገርን ይዞ ብቅ ሊል ይችላል።

ወራጅ ቀጠና ላይ ከሚገኙት ክለቦች ውጪ ሁለተኛ መጥፎ የተከላካይ መስመር ካላቸው ቡድኖች ተርታ የሚመደበው ጊዮርጊስ ከወገብ በላይ ያለው አቋሚ ከጨዋታ ጨዋታ እየተስተካከለ ይመስላል። በተለይ ደግሞ የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ እና አምበል በሆነው ጌታነህ ላይ የተገነባ የሚመስለው የቡድኑ የፊት መስመር አስፈሪነቱ እየጨመረ መጥቷል። ተጫዋቹም መስመር ላይ ከሚሰለፉት ተጫዋቾች ጋር ያለው መግባቦት እንዲሁም እነሱ የመጫወቻ ቦታ እንዲያገኙ በእንቅስቃሴ እና በኳስ ቅብብሎሽ ወደ መሐል የሚመጣበት ሒደት ለተጋጣሚ ተጫዋቾች እጅግ ፈታኝ ነው። በነገውም ጨዋታ እየተዋሃደ የመጣው የቡድኑ የአጥቂ መስመር ለፋሲል ከነማ የራስ ምታት ሊሆን ይችላል።

በግል ጉዳይ ምክንያት ፍሪምፖንግ ሜንሱን ብቻ የሚያጡት ፈረሰኞቹ በወልቂጤው ጨዋታ ተጎድቶ የወጣው አቤል እንዳለም ከጉዳት መልስ ማግኘታቸው ተሰምቷል።

ጨዋታው ውጥረት እንደሚኖርበት ቢገመትም ቡድኖቹ ባለፉት ጨዋታዎች ላይ ካሳዩት መጠነኛ የመከላከል ችግር እና ካላቸው ጠንካራ የማጥቃት ኃይል አንፃር ጎሎች ሊበዙበት እንደሚችል መገመት ይቻላል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን ለስምንት ያክል ጊዜ (ሁለት ፎርፌዎችን ጨምሮ) ተገናኝተዋል። ከስምንቱ ግንኙነት ቡድኖቹ ሦስት ሦስት ጊዜ ሲሸናነፉ ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። የፎርፌ ጎሎችን ጨምሮ ቅዱስ ጊዮርጊስ 11 ሲያስቆጥር ፋሲል ከነማ ደግሞ 10 ኳሶችን ከመረብ አገናኝቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ፋሲል ከነማ (4-2-3-1)

ሚኬል ሳማኬ

እንየው ካሳሁን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን

ሀብታሙ ተከስተ – ይሁን እንዳሻው

በረከት ደስታ – ሱራፌል ጌታቸው – ሽመክት ጉግሳ

ሙጂብ ቃሲም

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)

ለዓለም ብርሀኑ

ሄኖክ አዱኛ – አስቻለው ታመነ – ደስታ ደሙ– አብዱልከሪም መሀመድ

የአብስራ ተስፋዬ – ናትናኤል ዘለቀ

አቤል ያለው – አቤል እንዳለ – አማኑኤል ገብረሚካኤል

ጌታነህ ከበደ


© ሶከር ኢትዮጵያ