ሁለት አቻ ከተጠናቀቀው የሁለተኛ ዙር የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታ መገባደድ በኋላ አሠልጣኞች አስተያየታቸውን ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ – ድሬዳዋ ከተማ
ስለቡድኑ የመሻሻል ሂደት
ባለን ስብስብ እየሄድን ያለበት መንገድ ጥሩ ነው። የተወሰነ መሻሻል እንደሚያስፈልገን ጨዋታው ያሳያል። ነገር ግን እኔ የተደሰትኩት ከመጀመሪያው ጨዋታ ሁለተኛው ጨዋታ የተሻለ ነው። ወደ ጎል የምንሄድበት መንገድ በጣም ጥሩ ነው ፤ ግን ትንሽ ስል አይደለንም። እሱ ላይ የተሻለ ነገር መስራት ከቻልን ተወዳዳሪ የማንሆንበት ምክንያት የለም።
ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ቡድኑ በራሱ ሜዳ ስለመቅረቱ
እነሱ ኳስ ብዙ ስለሚይዙ መሀል ላይ ጠቅጠቅ ብለን ቀምተን በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ነበር ያቀድነው። እንዳጋጣሚ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻልንም። ነገር ግን መሀል ላይ ብዙ ኳሶች እንዳይነካኩ ለማድረግ ሞክረናል።
ስለቀጣይ ጨዋታዎች
እንደከዚህ በፊቱ ሰፊ የዝውውር ጊዜ ይኖራል ብለን አስበን ነበር። ሦስት ቀን ሁለት ቀን ናቸው እና እምብዛም ዝውውር ላይ እየሰራን አይደለም። ዝውውሩ ላይ በተለይም መሀል ሜዳ ላይ የተወሰነ መስራት ከቻልን ወደ ላይ ከፍ ማለት የማንችልበት ምክንያት የለም።
አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ – ሰበታ ከተማ
ጨዋታው እንደ ዕቅዳቸው ስለመሄዱ
የመጀመሪያው አጋማሽ ባሰብኩት መልኩ አልሄደም። ሁለተኛው ላይ የተሻለ ብልጫ ነበረን። ጎል የማግባት ችግር ነው የነበረብን። ያ ትንሽ ዋጋ አስከፍሎናል። ከዚህ በተረፈ ግን በአብዛኛው የጨዋታ ክፍል የእኛ ቡድን ያተሻለ እንቅስቃሴ አድርጓል ማለት ይቻላል። ነገር ግን በመጀመሪያው ጎሎች ገብተውብናል ውጤት ማስጠበቅ ላይ ችግር ነበረብን። እሱን ማስተካከል ይኖርብናል።
ኦሰይ ማወሊ መፈረሙ ስላለው ጥቅም
ማወሊ አግቢ ብቻም ሳይሆን ሰጪም ጭምር ነው። ሁለተኛ ደግሞ የእኛ ቡድን አጨዋወት ኳሱን ይዞ ወደ ተጋጣሚ ግብ መቅረብ ነው። ስለዚህ እዛ ቦታ ላይ ኳሱን ይዞ የሚቆይ ሰው ያስፈልገናል። ማወሊ ቡድናችንን መቀላቀሉ ማግባት ብቻ ሳይሆን በማጥቃት አጨዋወቱ ላይ የጎላ ሚና የኖረዋል ብዬ አስባለሁ።
ከክፍት ጨዋታ ጎል ማግኘት ስለመቸገሩ
አሁንም ባለፈው እንደተናገርኩት ነው። በእንቅስቃሴ የሚገቡ ጎሎችን ለማስቆጠር በቁጥር በልጠን ሳጥን ውስጥ እንደርሳለን። ነገር ግን ከሜዳችን ስንወጣ ከምናደርገው ጥንቃቄ አንፃር ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ የምናደርገው ጥንቃቄ አናሳ ነው። ስለዚህ እዛ ጋር የሚባክኑ ኳሶችን ለመቀነስ አሁንም ረጋ ማለት ይጠበቅብናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ