ፋሲል ከነማን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ባገናኘው የአስራ አራተኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ወሳኝ ጨዋታ ዙርያ ሄኖክ አዱኛ የሚናገረው አለው።
በዘንድሮው ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ወደ ዋንጫ የሚደረገውን ግስጋሴ ከሚጠቁሙ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የነበረው የዕለቱ ወሳኝ ፍልሚያ በፋሲል ከነማ እና በቅዱስ ጊዮርጊስ መካከል ተካሂዶ ዐፄዎቹ በያሬድ ባዬ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል አንድ ለምንም ማሸነፋቸው ይታወቃል። የዕለቱን ጨዋታ አስመልክቶ የፈረሰኞቹ ወሳኝ ተጫዋች ሄኖክ አዱኛ ከሶከር ኢትየጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።
” ስለ ዛሬው ጨዋታ ምንም ማለት አልፈልግም። በጣም ነው የሚያስጠላው፤ ስሜታችን ጎድቶታል። ጨዋታውን ለማሸነፍ በጣም ተዘጋጅተን ነበር የገባነው። እንዲህ ያለ ነገር ይፈጠራል ብለን አልጠበቅንም። ከመጀመርያው ጀምሮ ነው ዳኛው የተጫነን። ብዙ የኃይል አጨዋወት ፈቅዶ በመጨረሻ እንዲህ ያልተገባ ውሳኔ አሳለፈ። በጣም ነው የሚያሳዝነው። እያስፈራራን ነው የተጫወትነው። ከአንድ ዳኛ በማይጠበቅ ሁኔታ መልበሻ ክፍል መጥቶ ሁሉ የማይሆን ነገር ሲናገረን ነበር። ውድድሩ አላለቀም፤ ገና አስራ አንድ ጨዋታ ይቀራል። እኛም የቻልነውን ሁሉ አድርገን ቡድናችን የዋንጫ ባለቤት የሚሆንበትን ጥረት እናደርጋለን።”
© ሶከር ኢትዮጵያ