በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በዮርዳኖስ ምዑዝ ጎል ጌዲኦ ዲላን 1ለ0 አሸንፏል።
የመጀመሪያው አርባ አምስት ደቂቃ ሁለት ተቀራኒ መልክ ያለውን የጨዋታ አቀራረብ የተመለከትንበት ነበር፡፡ በእንቅስቃሴ ኤሌክትሪኮች በሙከራ ረገድ ግን ጌዲኦ ዲላዎች ተሽለው የታዩበት ነበር፡፡ አመዛኙ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ወደ መስመር ባደላ መልኩ ቡድኖቹ ሲጫወቱ ያስተዋልንበት ሲሆን የኤሌክትሪክ የመከላከል ድክመት ለጌዲኦ ዲላ አጥቂዎች ምቹ ሆኖ በይበልጥ የታየበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ 5ኛው ደቂቃ ላይ በዚህ የስህተት አጋጣሚ የተገኘችን ኳስ ከቀኝ በኩል ሰላማዊት ጎሳዬ ሰብራ ገብታ ከርቀት መታ ለጥቂት በወጣባት ሙከራ ዲላዎች ቀዳሚ መሆን ችለዋል፡፡
ይበልጡኑ ወደ ቀኝ መስመር ኮሪደሩ ተጠግቶ በእፀገነት ብዙነህ አማካኝነት ወደ ፊት ለመሄድ ሲጥሩ የነበሩት ኤሌክትሪኮች ምንም እንኳን በእንቅስቃሴ ከጌዲኦ ዲላ መሻል ቢችሉም የጠሩ የግብ ዕድሎችን ግን ማግኘት አልቻሉም፡፡ በአንፃሩ በተሻጋሪ ኳስ የኤሌክትሪክን የመከላከል አደረጃጀት በተደጋጋሚ ሲፈትኑ የተስተዋሉት ጌዲኦ ዲላዎች ተጨማሪ የግብ አጋጣሚን የአሰልጣኝ መሠረት ማኔ ልጆች በሰሩት የቅብብል ስህተት ይታገሱ ተገኝወርቅ አግኝታ አስቆጠረችው ሲባል ወደ ውጪ ሰዳዋለች፡፡
ከእረፍት መልስ ተመጣጣኝ ፉክክር በተደረጉበት ቀሪ አጋማሽ ክፍለ ጊዜ ጌዲኦ ዲላዎች አብዛኛው የኳስ ንክኪያቸው የሚቆራረጥ እንከኖች የበዙበት ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው የመሀል ሜዳ ክፍሉን በፂዮን ፈየራ አስገራሚ እንቅሴቃሴ በማጀብ ወደ ግራ መስመር በእፀገነት ብዙነህ ሌላ ግሩም እንቅስቃሴ በማጀብ ወደ ታታሪዋ አጥቂ ዮርዳኖስ ምዑዝ በማሻገር ጎል ለማስቆጠር ጥረቶችን አድርገዋል፡፡
70ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የሜዳ ላይ ቆይታ በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ የነበራት እፀገነት ብዙነህ ብልጠቷን ተጠቅማ የሰጠቻትን ኳስ በቅርቡ ከመቐለ ኤሌክትሪክን የተቀላቀለችሁ አጥቂዋ ዮርዳኖስ ምዑዝ በድንቅ የአጨራረስ አቅሟ ወደ ጎልነት ለውጣው ክለቧን መሪ አድርጋለች፡፡
ኤሌክትሪኮች ከዚህች ጎል መቆጠር በኃላ እፀገነት ለሣራ ሰጥታት ሳራ ብቻዋን አግኝታ ያመከነችው እና 81ኛው ደቂቃ ላይ ሳራ የሚያስቆጭ ዕድልን በድጋሚ አግኝታ የኤሌክትሪክን የጎል መጠን ከፍ የምታደርግበትን ዕድል ለሁለተኛ ጊዜ ስታዋለች፡፡ከሁለት ሙከራዎች በተጨማሪ ዮርዳኖስ ምዑዝ ሌላ አጋጣሚን አግኝታ አምክናዋለች፡፡በሁለተኛው አጋማሽ በሙከራ ረገድ ተቀዛቅዘው ሜዳ ላይ የታዩት ጌዲኦ ዲላዎች 1ለ0 ለመሸነፍ ተገደዋል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ዮርዳኖስ ምዑዝ የጨዋታው ምርጥ ተብላ ተመርጣለች፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ