ያለፉትን ተከታታይ አምስት ጨዋታዎች በመጀመርያ አሰላለፍ በመግባት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እያስመለከተን ከሚገኘው ከግብ ጠባቂው አብዱልከሪም ኑሪ ጋር ቆይታ አድርገናል።
በኢሉአባቡራ ገጠር ሱፔ በምትባል መንደር ተወልዷል። ይህች ገጠራማ መንደር ዕውቁ ደራሲ በዓሉ ግርማም የተወለደባት ከተማ ናት። ከልጅነቱ ጀምሮ የሆላንዳዊው ድንቅ ግብ ጠባቂ የቫንደርሳር አድናቂ በመሆን ግብ ጠባቂነትን እየወደደው እርሱን ለመሆን እየጣረ አድጓል። ከትውልድ ከተማው በመውጣት በመቱ ከተማ በትምህርት ቤት ውድድር በኋላም ለሦስት ዓመት በአንደኛ ሊግ (በብሔራዊ ሊግ) ተሳታፊ በሆነው መቱ ከተማ በመጫወት የግብ ጠባቂነት ህይወቱን በ2009 ጀምሯል። በባቱ ከተማ በተካሄደው የአንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ላይ ባሳየው ድንቅ ብቃት አሰልጣኝ ሻምበል መላኩ ዐይን ውስጥ በመግባት በ2012 የውድድር ዘመን በከፍተኛ ሊግ እየተሳተፈ ለሚገኘው ወሎ ኮምቦልቻ ውድድሩ በኮሮና ቫይረስ እስከተሰረዘበት ጊዜ ድረስ መጫወት ችሏል።
በመቀጠል ያለፉትን ዓመታት በጅማ አባ ጅፋር የግብ ጠባቂነት አሰልጣኝነቱን በጥሩ ኃላፊነት መንፈስ እየተወጣ የሚገኘው አሰልጣኝ መሐመድ ይህን ታዳጊ በማምጣት ለአባ ጅፋሮች እንዲጫወት አስችሎታል። በፕሪሚየር ሊግ የመጫወት ምንም ዓይነት ልምድ የሌለው አቡበከር ኑሪ ለአባ ጅፋር የመጀመርያውን ጨዋታ ለማድረግ ዕድል አግኝቶ በመጀመርያው ሳምንት ከአዳማ ከተማ ጋር ጨዋታ ለማድረግ ወደ ሜዳ ቢገባም ብዙም ሳይቆይ በተመለከተው ቀይ ካርድ ምክንያት ያገኘውን ዕድል እንዳይጠቀም ፈተና ሆኖበት ቆይቷል። በራስ መተማመኑን በማሳደግ እና ሁሌም ጠንክሮ በመስራት ራሱን የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ የሚጥረው አቡበከር ያለፉትን አምስት ሳምንታት የውጪ ሀገር ግብ ጠባቂ የሆነው ጃኮ ፔንዜን በማስቀመጥ ተስፋ ሰጪ ነገር ማሳየት ችሏል። በዛሬው ጨዋታም ምንም እንኳን ቡድኑ ከመመራት ተነስቶ በወልቂጤ ከተማ ሁለት ጎል ተቆጥሮበት ሽንፈት ቢያስተናገድም ከዚህ በላይ ጎሎች እንዳይቆጠሩ የበኩሉን ጥረት አድርጓል። ሶከር ኢርዮጵያ አበቡበከር ኑሪን ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አግኝታ አናግራዋለች።
በክለብ መታቀፍ ስለጀመረበት ሂደት
በፕሮጀክትም ሆነ በአካዳሚ ገብቼ አልተጫወትኩም። እንደ አጋጣሚ ለትምህርት ከተወለድኩባት ገጠራማ መንደር በ2009 ወደ መቱ መጥቼ አስራ አንደኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩኝ። በኋላ የብሔራዊ ሊግ ተሳታፊ ቡድን የሆነውን መቱ ከተማ ልምምድ ሲሰሩ እያየው ቆይቼ ዝምብዬ ልስራ ብዬ ገባሁ። በዛው የቡድኑ አባል በመሆን ለሦስት ዓመታት መጫወት ችያለሁ።
ዛሬ ስለገጠመው ሁኔታ
በጣም የሚገርመው ዛሬ መቱ ለሦስት ዓመት አብረውኝ የተጫወቱት የቀድሞ ተጫዋቾች ደውለውልኝ ነበር። ቡድናቸው ሊፈርስ መሆኑ በጣም አሳስቧቸዋል። ብዙ ወጣቶች አሉ እንደኔ መጫወት የሚችሉ። ይህ ክለብ መፍረሱ የብዙዎችን አቅም የሚያጨልም በመሆኑ በዚህ አጋጣሚ የከተማው ስፖርት አመራር ትኩረት እንዲያደርግላቸው መልዕክቴን አስተላልፋለሁ።
ወደ ሌላ ምዕራፍ ስለተቀየረው የግብ ጠባቂነት ህይወቱ
በመቱ እየተጫወኩ ለማጠቃልያ ውድድር ዝዋይ በነበርንበት ወቅት አሰልጣኝ ሻምበል መላኩ በእንቅስቃሴዬ ተደስተው ከፍተኛ ሊግ እንድጫወት ወደ ወሎ ኮምቦልቻ በ2012 ወሰዱኝ። ውድድሩ በኮሮና እስከተሰረዘበት ጊዜ ድረስ ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኩ ነበር። ከዛ ነው የጅማ አባ ጅፋር የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ መሀመድ ዘንድሮ ወደ ጅማ ይዞኝ የመጣው።
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያው ቀይ ካርዱ ትውስታ
አሰልጣኝ መሀመድ በእኔ አምኖብኝ የመጀመርያው ቋሚ ተሰላፊ እንድሆን አድርጎኝ ነበር። ያው ልምድ የለኝም ፤ በጣም ትልቅ ኃላፊነት በመሆኑ ጫናው ከባድ ነበር። በዚህ ሂደት ውስጥ ራሴን ለማሳየት ከፍተኛ ዝግጅት አድርጌ ብገባም ቀይ ካርድ አይቼ ወጣሁ። ቡድናችን በዛ ላይ ተቀያሪ ግብ ጠባቂ ያልነበረው በመሆኑ መልበሻ ክፍል ሁሉ ገብቼ በጣም ነበር ያለቀስኩት።
ቀይ ካርዱ በማየቱ በድጋሚ ዕድል አላገኝም ብሎ ስለአለመስጋቱ
በድጋሚ ዕድል እንደማገኝ እርግጠኛ ነበርኩ። የመጫወቱ ፍላጎት ስላለኝ እና ሁሌም የሚጎለኝን ስለምሰራ በድጋሚ ወደ መጫወቱ እንደምመለስ ተስፋ አድርግ ነበር። ያም ቢሆን አሰልጣኞቼ በእኔ ዕምነት ኖሯቸው ዕድልም ስለሰጡኝ አመሰግናለሁ።
በተከታታይ ጨዋታ የመሰለፍ ዕድል ስለማግኘቱ
ለኔ ትልቅ ልምድ ነው። በየጨዋታው ራሴን ለማሳደግ የምችለውን ጥረት እያደረኩ ነው። ይህን ዕድል ለእኔ ቀላል አይደለም። በብሔራዊ ሊግና በከፍተኛ ሊግ ነው የተጫወትኩት። በአንዴ ይህን ዕድል ማግኘት ከባድ ቢሆንም እኔ አግኝቻለሁ። የህን አጋጣሚ ለመጠቀምም ከዚህም በኋላ ሁሌም ጠንክሬ እሰራለሁ።
የውጪ ግብ ጠባቂ ማስቀመጥ ያለው ስሜት
ያው ብዙ የተለየ ነገር የለውም። በነገራችን ላይ ጃኮ በጣም ነው የሚያግዘኝ ፤ በልምምድ ወቅት ማስተካከል የሚገባኝን ነገር ይነግረኛል። በጣም ጎደኛዬ ነው። በዚህ አጋጣሚ ላመሰግነው እፈልጋለሁ። ከውጪ እንደ ቫንደርሳር ሁሉ የዴቪድ ዴሂያ በጣም አድናቂ ነኝ። የእርሱን ቪዲዮ በጣም ነው የማየው ፤ የሌሎችንም እከታተላለው። ስለዚህ ብዙም የተለየ ነገር የለውም።
በሊጉ ልምድ የሌለው መሆኑ ስለፈጠረበት ነገር
አዎ ከከፍተኛ ሊግ ነው የመጣሁት በፕሪሞየር ሊግ የመጫወት ልምድ የለኝም። ይህ ከባድ ሊሆን ይችላል። ግን ገና ወጣት ግብ ጠባቂ ስለሆንኩ የሚሰማኝ ምንም ዓይነት ፍራቻ የለም። ዋናው እኔ ለአላማ ጠንክሮ መስራት ስለሆነ እና የመጫወት ከፍተኛ ፍላጎት ስላለኝ በዛ ላይ የግብ ጠባቂው አሰልጣኝ መሐመድ በጣም ስለሚረዳኝ ማስተካከል ያለብኝ ነገር እየነገረኝ እዚህ ደርሻለው።
በቀጣይ ስለሚያስበው
አሁን የማስበው ጅማን መታደግ ነው ፤ መጀመርያ እርሱ ነው ሀሳቤ። ከቡድን አጋሮቼ ጋር ጠንክሬ ሰርቼ ቡድኑን መታደግ አስባለሁ። ከዛም የራሴ ዕቅዶች አሉኝ ፤ ፈጣሪ ካለ ሀገሬን ማገልገል እፈልጋለው። ለዚህም የማስብበት ቦታ ለመድረስ ብዙ መስራት አለብኝ። ቦግ እልም ሳይሆን ለብዙ ዓመት መጫወትን አስባለሁ። ለአንድ ሁለት ዓመት ሳይሆን ከአስር ዓመት በላይ መጫወት እፈልጋለው።
በአንድ ወቅት ስለገጠው ገጠመኝ
አንድ ክለብ ለሙከራ ሄጄ ነበር። አዩኝ እና ‘ከየት ነው የመጣኸው ?’ አሉኝ። ‘ከየት ብመጣ ምን ይጠቅማችኋል ? ዋናው ወቅታዊ አቋሜ ነው።’ አልኳቸው። ‘እምቢ ከብሔራዊ ሊግ የመጣን አንፈልግም’ ብለው ሳያዩኝ መለሱኝ። በጊዜው በጣም ተሰምቶኝ አዝኜ ነበር። ያው ጠንክሬ ሰርቼ እነርሱን ማሳፈር እንዳለብኝ ውስጤን አሳምኜ ይህው ጠንክሬ ሰርቼ እዚህ ደርሻለው።
በመጨረሻም…
ብዙ አልተነገረትም ሆኖም እጅግ አስገራሚ ሥራዎችን እየሰራ ነው። በጣም የሚከበር ጠንካራ ሰው ነው። ያለውን ልምድ ሳይሳሳ የሚሰጥ መልካም ሰው ነው። በዚህ አጋጣሚ የግብ ጠባቂ አሰልጣኜ መሐመድን በጣም እንደማከብረው እና እንደማመሰግነው መግለፅ እወዳለሁ። እናንተም እንዲህ ያለን ሰው ቃለመጠይቅ በማድረግ ልታበረታቱት ይገባል።
© ሶከር ኢትዮጵያ