ባህር ዳር ከተማ ሲዳማ ቡናን ከመመራት ተነስቶ 2-1 ሲያሸንፍ የማሸነፊያውን ጎል ያስቆጠረው ወሰኑ ዓሊ ከጨዋታው በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።
በአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመሩት ባህር ዳር ከተማዎች የሁለተኛ ዙር የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ከሲዳማ ቡና ጋር አከናውነው ድል ተቀዳጅተዋል። ቡድኑ ከመመራት ተነስቶ ሦስት ነጥብ ሲያገኝ የወሰኑ ዓሊ የማሸነፊያ ጎልም ወሳኝ ነበረች። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም የቡድኑን ከአራት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ድል እንዲያገኝ ያስቻለችውን ኳስ የሲዳማው የግብ ዘብ መሳይ አያኖ ላይ ያስቆጠረው ወሰኑ ዓሊ ተከታዩን ብሎናል።
“የዛሬው ጨዋታ በጣም ጥሩ ነበር። ካለን አቅም አንፃር አሁን ላይ ያለንበት ደረጃ እኛን የማይመጥን ነው። ያንንም ለማስተካከል በሜዳ ላይ ተንቀሳቅሰናል። በጨዋታውም ያሰብነው ነገር በተወሰነ መልኩ ተሳክቶልናል።
“የማሸነፊያዋን ጎል በማስቆጠሬ በጣም ደስ ብሎኛል። ከምንም በላይ ግን አሠልጣኛችን (ፋሲል ተካልኝ) የቡድኑ ውጤት እንዲስተካከል እና እኛ ወደ ጎል አግቢነት እንድንመለስ በጣም ሲለፋብን ነበር። እንደ አጋጣሚም ሆኖ እኔ ግቡን አስቆጠርኩ እንጂ የቡድኑ ጥረት ነው ግቡን ያስገኘው። በአጠቃላይ ግቡን በማስቆጠሬ የተለየ ስሜት ተሰምቶኛል።
“በሊጉ ጥሩ ተፎካካሪ ሆኖ የመቅረብ እና በደረጃ ሠንጠረዡ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ቦታ የመያዝን ዓላማ ሠንቀን ነው እየተጫወትን ያለነው። ከዚህ በኋላ ያሉትንም ጨዋታዎች በተቻለን መጠን ለማሸነፍ እንሞክራለን።
“ደጋፊዎች ሁሌም የተሻለ ነገር ይፈልጋሉ። እነሱ ቡድኑ እንዲሻሻል እንደሚፈልጉ ሁሉ እኛም ቡድኑ የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲሆን እንፈልጋለን። በተለይ አሁን ግን የእነሱ እርዳታ በጣም ያስፈልገናል። እስካሁንም ከጎናችን ነበሩ። ከዚህም በኋላ እንዳይለዩን አደራ ማለት እፈልጋለሁ።
“በስተመጨረሻ አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝን እና የቡድን አጋሮቼን ማመስገን እፈልጋለሁ። የዛሬው ውጤት እንዲገኝም የሁሉም አስተዋፅኦ ነበር።”
© ሶከር ኢትዮጵያ