በመጀመርያው ዙር ባጋጠመው ጉዳት ከሜዳ ርቆ ወደ ሜዳ የተመለሰው ይገዙ ቦጋለ ስለ ዛሬ ስላጋጠመው ጉዳቱ ይናገራል።
ሲዳማ ቡና ወደ ሊጉ ከመጣበት ጊዜ አንስቶ አጋጥሞት የማያቀው የውጤት ቀውስ ውስጥ ሆኖ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። የቡድኑ ውጤት ማጣት እንዳለ ሆኖ የቡድኑ ወሳኝ አጥቂ የሆነው ይገዙ ቦጋለ በመጀመርያው ዙር ከአዳማ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ ከፍተኛ ጉዳት አስተናግዶ ከሜዳ በመውጣቱ ለሁለት ወር ቡድኑን ማልገል ሳይችል ቀርቷል።
በዛሬው የባህር ዳር ጨዋታ የቡድኑ የመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ በመካተት ወደ ሜዳ መመለስም የቻለው ይገዙ በጨዋታው ላይ መቆየት የቻለው ለ13 ደቂቃ ብቻ ነበር። ሲዳማ ቡና በፍፁም ቅጣት ምት ላስቆጠራት የመሪነት ጎል መነሻ ምክንያቱ ሆኖ የነበረ ቢሆንም ግጭቱ ታፋው ላይ የመሰንጠቅ አደጋ እንዲደርስ እና ተቀይሮ እንዲወጣ አስገድዶታል።
እንደታሰበው በጉዳት ምክንያት ቡድኑን ማገልገል ያልቻለው ይገዙ ቦጋለ ስለጉዳቱ ሁኔታ ለሶከር ኢትዮጵያ ተከታዩን ተናግሯል።
” ይህ ዓመት ለኔ ፈታኝ ነው። ያለፉትን ዓመታት በጥሩ አቋም ቡድኔን ማገልገል ችያለሁ። ዘንድሮም ሲዳማ ቡና ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግብ የተለየ ዝግጅት አድርጌ ነበር። ጨዋታውም በዲኤስ ቲቪ የሚተላለፍ መሆኑ የበለጠ ራሴን በማሳየት ለብሔራዊ ቡድን መጫወት አስብ ነበር። ባለፈው ከአዳማ ጋር በነበረ ጨዋታ ጉዳት አስተናግጄ ለሁለት ወር ከሜዳ ርቄ ነበር። ቡድናችን ያለበት ሁኔታ ያሳስበኛል። ለዛም ነው በተለያዩ ጊዜያት አለቅስ እበሳጭ የነበረው። ዛሬም ከወራት በኃላ ከጉዳቴ አገግሜ እየተጫወትኩ ባለሁበት ሰዓት ሌላ ጉዳት አስተናግጃለው። ዘንድሮ እድለኛ አይደለሁም። ሲዳማ ቡና ከፈጣሪ ቀጥሎ እኔን እዚህ ደረጃ ያደረሰኝ አሳዳጊዬ ክለብ ነው። አሁን ያለበት ሁኔታ ያሳስበኛል። ሁሉንም ነገር የማደርገው ለቡድኑ ካለኝ ፍቅር ተነስቼ ነው። ፈጣሪ የፈቀደው ነው የሚሆነው። ዶክተሩ ከአንድ ሳምንት በኃላ ወደ ሜዳ እንደምመለስ ነግሮኛል። ዳግመኛ ወደ ሜዳ ተመልሼ ቡድኔን እንደማገለግለል ተስፋ አድርጋለሁ።”
© ሶከር ኢትዮጵያ