ቀጣዩ የዳሰሳችን ትኩረት ነገ ከሰዓት የሚከናወነው ጨዋታ ይሆናል።
የዓመቱ ሁለተኛ ድሉን በአዳማ ላይ ያሳካው ጅማ አባ ጅፋር ወደ ባለሁለት ቁጥር የነጥብ ስብስብ ቢያድግም አሁንም ከስጋት ለመላቀቅ ብዙ ርቀት መጓዝ ይጠበቅበታል። ጅማ ነገ ማሸነፍ ከቻለ ከቀጠናው ባይወጣም በዚህ ሳምንት አራፊ የሆነው ሲዳማን ቦታ መውሰድ ይችላል። ከሰንጠረዡ አጋማሽም መንሸራተት የጀመረው ወልቂጤ ከተማ ከሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ጅማን ይገጥማል። ድል ፊቷን ያዞረችበት ቡድኑ ከዚህ ጨዋታ መሉ ነጥብ አሳክቶ ከፍ ማለት ካልቻለ መነቃቃት እያሳዩ የሚገኙ ቡድኖች ወደ ታች እየገፉት ለወራጅ ቀጠናው ትግል እንዳይጋለጥ ያሰጋዋል።
በአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ስር ጥሩ መነቃቃት እያሳየ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር አልፎ አልፎ ከሚታይበት መዘናጋት ውጪ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀቱ ወደ ነገው ጨዋታ የሚወስደው ጠንካራ ጎኑ ነው። ኳስ መያዝ ምርጫቸው ለሆኑ ቡድኖች እምብዛም ከሜዳው ሳይወጣ ክፍተቶችን መዝጋት ምርጫው እያደረገ የመጣው ቡድኑ ነገም ተመሳሳይ አካሄድን እንደሙከተል ይጠበቃል። እንደ አብዱል ከሪም ወርቁ ያለ ባለ ተሰጥኦ አማኮዮችን ከማቆም አንፃርም በዉጥነት እያገለግለ ከሚገኘው ንጋቱ ገብረስላሴ በተጨማሪ አዲስ ፈራሚው አማኑኤል ተሾመ በቶሎ ከቡድኑ ጋር መዋሀዱ ተጠቃሚ ያደርገዋል። ፊት መስመር ላይም ከመልሶ ማጥቃት የሚገኙ ዕድሎችን ለመጠቀም የሳዲቅ ሴቾ መነቃቃት ለአሰልጣኝ ፀጋዬ ቡድን በጥንካሬ የሚነሳለት ነው። ቡድኑ አሁን ባለበት ሁኔታ ግን ቀድሞ ግብ ካስተናገድ ከጥንቃቄ አዘል አቀራረቡ ወጥቶ ግብ ፈለጋ ላይ ትኩረት ለማድረግ ሲሞክር ክፍተቶችን ፈጥሮ ለተደጋጋሚ ጥቃት እንዳይጋለጥ ያሰጋዋል።
ነገ ለሠራተኞቹ እና ለአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው እጅግ ወሳኝ የጨዋታ ቀን ነው። መጥፎ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ባያደርግም ከፊት በደካማ አጨራረስ ከኋላ ደግሞ በግለሰባዊ ስህተቶች ምክንያት ተደጋጋሚ ሽንፈቶች እያገኙት ያለው ወልቂጤ ወደ ውጤት የመመለስ ጫና ውስጥ ሆኖ ጅማን ይገጥማል። ከቡድኑ ውጤት በተቃራኒ እጅግ ድንቅ ጊዜ እያሳለፈ በሚገኘው አብዱልከሪም ወርቁ መሪነትም እንደ ቡናው ጨዋታ መሀል ሜዳ ላይ ብልጫ ለመውሰድ ብዙ ፉክክር ባይገጥመውም የሜዳውን አጋማሽ አልፎ የግብ ዕድሎችን የሚያስገኙ ክፍተቶችን መፍጠር ትልቁ ፈተናው እንደሚሆን ይጠበቃል። ከዛም ባለፈ በግብ ፊት ያለው የቡድኑ አጨራረስ መውረድ እንደመጀመሪያው ዙር የዚህ መርሐ ግብር ጨዋታ ሁሉ ዕድሎችን በማብከኑ ከቀጠለ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጫናው በርትቶ ግብ የማግኘት አጋጣሚውን ይበልጥ ሊቀንሰው ይችላል። የዛኑ ያህል በቶሎ ኳስ እና መረብን ማገናኘት የጨዋታውን ክብደት ሊያቀልለት እንደሙችልም ይታሰባል። ከምንም በላይ ግን የመከላከል ጥንካሬው ትዝታ ብቻ እየሆነ የመምጣቱ ነገር ካልተስተካከለ እና ነገም ግብ ካስተናገደ ፈተናው እጥፍ መሆኑ የማይቀር ነው።
በጨዋታው ጅማ አባ ጅፋር አጥቂው ብዙአየሁ እንዳሻው ከጉዳት ያገገመለት ሲሆን ወንድምአገኝ ማርቆስን በአምስተኛ ቢጫ ካርድ ቅጣት ከማጣቱ በቀር ቀሪ ስብስቡ ለጨዋታው ዝግጁ ነው። አዲስ ፈራሚው ስዩም ተስፋዬም የወንድምአገኝን የቀኝ መስመር ተከላካይ ቦታ በመሸፈን በነገው ጨዋታ ዕድል ሊያገኝ ይችላል። ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው የመጨረሻ የቅጣት ቀኑን በሚያሳልፍበት ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ አሳሪ አልመሀዲን እና ፍሬው ሰለሞን በጉዳት ምክንያት የሚያጣቸው ሌሎች ተጨዋቾቹ ሆነዋል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ክለቦች በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙበት የዘንድሮው የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታ ያለግብ የተጠናቀቀ ነበር።
ግምታዊ አሰላለፍ
ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)
አቡበከር ኑሪ
ሥዩም ተስፋዬ – መላኩ ወልዴ – ውብሸት ዓለማየሁ – ኤልያስ አታሮ
አብርሀም ታምራት – አማኑኤል ተሾመ – ንጋቱ ገብረሥላሴ
ተመስገን ደረሰ – ሳዲቅ ሴቾ – ሱራፌል ዐወል
ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)
ዮሐንስ በዛብህ
ተስፋዬ ነጋሽ – ቶማስ ስምረቱ – ተስፋዬ መላኩ – ረመዳን የሱፍ
ያሬድ ታደሰ – ሀብታሙ ሸዋለም – አብዱልከሪም ወርቁ
አቡበከር ሳኒ – ሄኖክ አየለ – አሜ መሐመድ
© ሶከር ኢትዮጵያ