የሊግ ካምፓኒው በቀጣይዋ አዘጋጅ ከተማ ዙርያ ውሳኔ አሳለፈ

የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ በቀጣይ በምታስተናግደው ድሬዳዋ ከተማ ዙርያ ዛሬ ባደረገው ስብሰባ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።

ቦሌ በሚገኘው አዲሱ ቢሮ በተካሄደው የሊግ ካምፓኒው የቦርድ ስብሳባ በቀጣይ አራተኛውን ንዑስ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ውድድር በምታስተናግደው ከተማ ዙርያ ከስምንት ሰዓት ጀምሮ ውይይት ማድረጉን ሰምተናል።

ድሬዳዋ ውድድሩን ለማስተናገድ በምን ቁመና ላይ እንደምትገኝ በሁለት ዙር ግምገማ ያደረገው የሊግ ካምፓኒው ልዑክ ቡድን ሪፖርቱን ያቀረበ ሲሆን በአብዛኛው መስፈርቶች ከተማዋ ውድድሩን ለማስተናገድ የሚያስችላት ሁኔታዎች እንዳሉ ማረጋገጡን ገልጿል።

ሆኖም ውድድሩን በምሽት ለማድረግ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ እና ሙያዊ ክትትል ለማድረግ የሊግ ካምፓኒው የልዑክ ቡድን ለሦስተኛ ጊዜ የፊታችን ቅዳሜ ወደ ድሬደዋ እንደሚያቀና ለማወቅ ችለናል።

ድሬዳዋ ካላት ከፍተኛ የሙቀት መጠን ጋር በተያያዘ በተለየ ሁኔታ ጨዋታዎቹን በምሽት ለማድረግ የፓውዛ ተከላ እና የጄኔሬተር ግዢ መፈፀሟ ይታወቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ