የሳምንቱ ጨዋታዎችን ተመርኩዘን የተመለከትናቸው አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮች እና ዐበይት አስተያየቶች እንደሚከተለው አቅርበናል።
👉 ማሒር ዴቪድስ እና የተጫዋቾች ምርጫ
በዘንድሮው የውድድር ዓመት ባልታሰበ ሁኔታ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝነት የመጡት ደቡብ አፍሪካዊው ማሂር ዴቪድስ የቡድን ግንባታቸው ባሰቡት መልኩ እየሰመረላቸው አይገኝም። የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ በሊጉ የአስራ ስድስት ሳምንታት ጉዞ ቋሚ ቡድናቸውን ለመወሰን የተቸገሩም ይመስላሉ። ቡድኑ በስብስብ ጥራቱ ከሊጉ ክለቦች የላቀ መሆኑ ለሁሉም ተጫዋች በቂ የመጫወቻ ጊዜ ለመስጠት ያሰበ በሚመስል መልኩ በስብስቡ ከሚገኙ ተጫዋቾች መካከል ከሳላዲን በርጊቾ እንዲሁም ወጣቶቹ አብርሀም ጌታቸው እና ዳግማዊ አርዓያ በቀር ለሌሎቹ የመሰለፍ ዕድል ሰጥተዋል።
በተለይም በአማካይ ክፍል ላይ የሚያደርጉት ምርጫ በውድድር ዓመቱ ወጥ መልክ ያልያዘ ሲሆን በቅርብ ጨዋታዎች የታየው የናትናኤል – አቤል – ያብስራ ጥምረት በሀዋሳው ጨዋታ በናትናኤል – ከነዓን – ሀይደር ተተክቶ ታይቷል። በንፅፅር ከተከላካይ ክፍሉ እና ከፊት አጥቂው ጌታነህ ከበደ ውጪም ቡድኑ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ የሚጠቀማቸው ተጫዋቾች ተለዋዋጭነት በተለይም ከፋሲል እና ኢትዮጵያ ቡና ጋር ሲተያይ በእጅጉ ወጥነት የጎደለው ሆኖ እንደቀጠለ ነው። ለዚህም ይመስላል ጊዮርጊስ የተዋጣለት እና በድግግሞች የሰለጠን የማጥቃት ዕቅድ ይዞ የማይታየው። በውጤቱም በቂ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር አቅሙ በተለይም ጠንከር ካሉ ቡድኖች ጋር ሲገናኝ መቀዛቀዙ ነጥቦችን እንዲያጣ እያደረገው ነው። ከዚህ በተለየ በአስተያየቶቻቸው በቡድኑ የግንባታ ሒደት ደስተኛ ሆነው የሚያዩት አሰልጣኝ ማሒር ከዕረፍቱ በኋላ በምን አኳኋን ይመለሳሉ የሚለው የሚጠበቅ ጉዳይ ነው።
👉 አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በባህር ዳር አልተሳካላቸውም
በዚህ ሳምንት ከተደረጉ ጨዋታዎች መካከል ሀዲያ ሆሳዕና ሲዳማ ቡናን 2-0 ያሸነፈበት ጨዋታ ተጠቃሽ ነው። ሽንፈቱ ሲዳማ በአዲሱ አሰልጣኙ ስር ያስመዘገበው አራተኛ ተከታታይ ሽንፈት ሆኖም አልፏል። የሁለት ጊዜ የሊጉ ቻምፒዮን አሰልጣኝ ከሀዲያው ጨዋታ ውጪም የተረከቡት ኃላፊነት ቀላል አለመሆኑን የሚያሳዩ ሳምንታትን ነው በባህር ዳር ያሳለፉት። አሰልጣኙ የቡድኑን በቶሎ ወደ ውጤት አለመመለስ ከሥነ -ልቦና ጋር ቢያገናኙትም ሜዳ ላይ የሚታየው እንቅስቃሴ ግን በውህደት ደረጃም ሲዳማ ብዙ ክፍተት እንዳለበት ያሳየ ነበር።
ሀዲያ ሆሳዕናን ሲገጥሙ በመጀመሪያ አሰላለፋቸው ውስጥ አምስት አዳዲስ ተጫዋቾቻቸውን የተጠቀሙት አሰልጣኝ ገብረመድህን በቀድሞው አጥቂያቸው ኦኪኪ አፎላቢ መመራትን ምርጫቸው አድርገው ነበር። ያም ቢሆን ቡድኑ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጫና ፈጥሮ ለመጫወት ከመሞከሩ ውጪ የተጋጣሚውን የኋላ መስመር መስበር ከብዶት ታይቷል። በእንቅስቃሴም ለውህደት ብዙ ርቀት እንደሚቀረው በቀላሉ መናገር ይቻላል። ከዚህ አንፃር የቅርብ ጊዜ የቻምፒዮንነት ታሪክ ያላቸው አሰልጣኙ በሌላ የውጤት ፅንፍ ላይ ባለው ፉክክር ውስጥ ስኬታማ ይሆናሉ ለማለት በዕረፍት ጊዜው ቡድናቸውን አዋቅረው የሚመጡበትን መንገድ የምንጠብቅ ይሆናል።
👉 አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ከፈተና ወደሌላ ከባድ ፈተና
ከሲዳማ ቡና ጋር ጥሩ የውድድር ዓመታትን አሳልፈው ዘንድሮ ሳይሳካላቸው የቀሩት አሰልጣኝ ዘርዓይ በውድድሩ አጋማሽ ሌላ ከባድ ኃላፉነትን መሸከም ምርጫቸው አድርገዋል። በአዲሱ ሥራቸው ከቀደመው ክለባቸው ሲዳማ ቡና በስብስብም ሆነ በሥነ-ልቦና ይበልጥ የተዳከመው አዳማ ከተማን የተረከቡ ቢሆንም ቡድኑን በማትረፉ ረገድ ከመጀመሪያው ጨዋታ በፊት በሰጡት አስተያየት ይታይባቸው የነበረው እርግጠኝነት እየሸሻቸው ያለ ይመስላል።
ከስብስብ አንፃር መሻሻሎችን ለማድረግ ወደ ገበያ የወጣው አዳማ ከተማ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ቢያስፈርምም አሰልጣኙ ለማምጣት ላሰቡት ለውጥ በቂ አለመሆኑን ሲያነሱም ይሰማል። በዚህ ሳምንት በባህር ዳር ከተማ ሲሸነፉ ከአዳዲሶቹ አራቱን በመጀመሪያ አሰላለፋቸው ውስጥ ያስገቡት አሰልጣኙ ሀብታሙ ወልዴን ደግሞ ከተጠባባቂነት በማስነሳት ተጠቅመዋል። ከጨዋታው በኋላ የሰጡት አስተያየት ግን በነባሮቹም ሆነ በአዲሶቹ ተሰላፊዎቻቸው ደስተኛ አለመሆናቸው ሲታይ ተጨማሪ ተጫዋቾችን ወደ መጨመሩ ያመዘነ ይመስላል። ነገር ግን ደካማም ቢሆን አብሮ በመቆየት የተሻለ ከነበረው የሲዳማው ቡድናቸው በውድድር አጋማሽ በበርካታ አዳዲስ ተጫዋቾች አሰባስቦ እንደአዲስ እየተዋቀረ ወዳለው የአዳማ ኃላፊነት መምጣታቸው ፈተናውን ከፍ ያደረገባቸው ይመስላል።
ዓበይት አስተያየቶች
👉ካሣዬ አራጌ ስለአሥራት እና እንዳለ ግብ ማስቆጠር
“አዎ ጥሩ ነው። እኛ በምንጫወተው ጨዋታ ውስጥ የመጨረሻ ኳስ የሚጠይቁ ሰዎች እንዲበዙ እንፈልጋለን። ያ ለተጋጣሚ ከኋላ ለሚጫወቱ ተጫዋቾች አስቸጋሪ ነው ብለን ስለምናስብ። አንዱ ማረም የነበረብን እሱ ነው። ወደፊትም የመጨረሻ ኳስ የሚጠይቁ ሰዎች አቡኪ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም መጨመር አለባቸው። ያ ጥሩ አጋጣሚ ነበር።”
👉ማሒር ዴቪድስ በባህር ዳር ስለነበረባቸው ድክመት
“በጨዋታ ረገድ ጥሩ ነበርን። ጨዋታዎችን መግደል ላይ ነበር ድክመታችን። የዛሬው ጨዋታ አንዱ ምሳሌ ነው። ወደ ፋሲሉ ጨዋታም ብትሄድ ማሸነፍ የምንችልባቸው ዕድሎች ኖረው በሽንፈት ጨርሰናል። ከድሬዳዋ ጋርም እንዲሁ ዕድሎች ኖረውን ነጥብ ተጋርተናል። ዛሬም ሁለት ሦስት ያለቀላቸው አጋጣሚዎች ነበሩን ፤ ግን አላደረግነውም። በመጨረሻም ነጥብ ተጋርተናል።”
👉ሥዩም ከበደ ስለቡድኑ የእስካሁኑ ጠንካራ ጎን
“አንደኛ የኳስ ቁጥጥሮች እየተሻሻሉ ሄደዋል። ሁለተኛ እንደቡድን የመከላከል ብቃታችን ጥሩ ነው። በተጨማሪ ደግሞ ተቃራኒ ሜዳ ገብተን የምናደርጋቸው ሙከራዎች በጣም ጥሩ ናቸው። እንደዛም ሆኖ የምንስታቸው አሉ። ለምሳሌ በመጀመሪያው አጋማሽ 3-0 ማረፍ እንችል ነበር። እንደነበረከት ያገኙትን ለመጨረሰ 100% ትኩረት ማድረግ አለባቸው። እነዚህ ነገሮች የሚሻሻሉ ቢሆንም በቡድኑ ላይ ግን ከፍተኛ ለውጦች ናቸው ብዬ አስባለሁ።”
👉አሸናፊ በቀለ ወደ ዋንጫው ፉክክር ስለመመለስ
“ሀዲያ በተከታታይ ሁለት ጨዋታ መሸነፉ ከለመደው ባህል ውጪ ነው። በተለይ ተከላካይ መስመራችን ላይ ወሳኝ የምንላቸው ተጫዋቾች አለመኖራቸው እና ቡድናችን ተሟልቶ ያለመግባቱ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥሮብናል። ሆኖም ግን አሁን የዑመድ መምጣት በቡድናችን ላይ የፈጠረው መነሳሳት አለ። ከጨዋታ የራቀ ተጫዋች ነው። ግን በሂደት ቡድኑ ላይ ሰርተን የተሻለ ውጤት አምጥተን ሜዳሊያ ውስጥ ሆነን ለመጨረስ የሚቻለንን ሁሉ እናደርጋለን።”
👉ገብረመድህን ኃይሌ ቡድኑን ለመገንባት ጊዜ ስለማስፈለጉ
“ያስፈልጋል አዎ ! ትንሽ ጊዜ አገኘን ቢባል ያሁኑ ስምንት ቀናት ናቸው። ከዛ በፊት በየአራት ቀኑ ጨዋታ ነው። ምንም ዓይነት ዝግጅት አላደረግንም። ተጫዋቾቹን ለማወቅ በጣም ከባድ ነው። አሁን ግን ሁሉንም ተጫዋቾች አውቄያለሁ ማለት ይቻላል። ከዚህ ቀጥሎ ያለው የዕረፍት ጊዜ ትንሽ ይረዳናል ብለን እናስባለን። እንግዲህ አሻሽለን ከዚህ ከአደጋው ለማምለጥ ጥረት እናደርጋለን።”
© ሶከር ኢትዮጵያ