የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

የአስራ ስድስተኛ ሳምንት ዐበይት ትኩረት አራተኛ ክፍልን እነሆ!

👉የባህር ዳር ከተማ ቆይታ መጠናቀቅ

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የእስካሁኑ የ16 የጨዋታ ሳምንታት ጉዞው በሦስት የተለያዩ ከተማዎች ተከናውኗል። በአዲስ አበባ ስታዲየም እና ጅማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ከተደረጉት ውድድሮች በመቀጠል የማስተናገድ ዕድሉን ያገኘችው ባህር ዳር ከበርካቶች ሙገሳን ያስገኘ ዝግጅት አከናውና በዚህ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎችን በማስተናገድ ለተተኪዋ ድሬዳዋ ግዳጁን አስረክባለች።

የባህር ዳር ዝግጅት በስታዲየሙ ጥራት እና የመጫወቻ ሜዳ ምቹነት፣ በሆቴል አቅርቦት፣ የእንግዳ መቀበል ልምድ እና በመሳሰሉት ሲመዘን በሀገሪቱ ደረጃ የተሟላ ለማለት የሚያስችል ነበር።

በከተማዋ የአምስት ሳምንት ጨዋታዎች የተደረጉ ሲሆን ፋሲል ከነማ በግስጋሴው የቀጠለበት፣ ባህር ዳር ከተማ፣ ሰበታ ከተማ እና ወላይታ ድቻ እንዲሁም የሦስቱን ያህል ባይሆንም ጅማ አባ ጅፋር ከፍተኛ መሻሻል ያሳዩበት ሆኖ አልፏል። እንደ ሲዳማ፣ አዳማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የመሳሰሉት ደግሞ ደካማ ጊዜ ያሳለፉበት ከተማ ሆኗል።

👉የቀለም ስብጥር በክለቦች መለያ ላይ

በሀገራችን የክለቦች መለያ ጋር በተያያዘ የመለያዎች ቀለም እና በመለያዎቹ ላይ ቁጥሮች እና ሌሎች ፅሁፎች የሚፃፉባቸው የቀለማት ምርጫ ላይ ጥያቄዎች ይነሳሉ። በትኩረት ዐምዳችን ላይም በተደጋጋሚ ከዚህ ጋር በተያያዘ አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን ስናነሳ ቆይተናል።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በተለይ ኢትዮጵያ ቡና ድሬዳዋ ከተማን ሲገጥም በቡናማው መለያቸው ላይ የተጫዋቾች ስም በጥቁር ቀለም እንዲሁም ሲዳማ ቡና ሀዲያ ሆሳዕናን ሲገጥሙ በተጠቀሙት አረንጓዴ መለያ ላይ በተመሳሳይ በጥቁር ቀለም የተፃፈው የተጫዋቾች የመለያ ቁጥር እና ስም ለተመልካች ለእዕታ እጅግ አዳጋች የነበሩ ናቸው።

እንደ ሌሎች ሀገራት ሊጎች ይህን ጉዳይ በተመለከተ ህጎች አለመኖሩን ተከትሎ ቡድኖች ለተለያዩ ፅሁፎች የሚውሉ የቀለም ምርጫዎችን በሚያደርጉበት ወቅት የክለቡን ቀለማት እንዲሁም በተቀዳሚነት ከመለያው ቀለም ጋር ለመጠቀም ያሰቡት የቀለም አይነት የሚፈጥረው ህብር ከዕይታ አመቺነት አንፃር ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

👉 የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች ድጋፍ አሰጣጥ

በዚህ የጨዋታ ሳምንት ትኩረት ከሳቡ ሁነቶች መካከል የሲዳማ ደጋፊዎች የድጋፍ አሰጣጥ አንዱ ነው። በተከታታይ ሽንፈቶች ወደ ሊጉ ወራጅ ቀጠና የተቀላቀለው ሲዳማ ቡና በ16ኛው ሳምንትም በሀዲያ ሆሳዕና 2-0 ተረትቷል። እምብዛም በጨዋታዎች ላይ የማይታዩት የክለቡ ደጋፊዎችም በባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታድየም በውስን ቁጥር ተገኝተው ቡድናቸውን ለማበረታታት ሞክረዋል። ነገር ግን የፈለጉትን ውጤት አለማግኘታቸው እና በቡድናቸው እንቅስቃሴም ደስ አለመሰኘታቸው ከመስመር የወጣ ተቃውሞ ውስጥ አልከተታቸውም። በሊጋችን በተደጋጋሚ በዳኞች ውሳኔ እና በቡድኖች አቋም የተከፉ ተመልካቾች ተገቢ ያልሆኑ ቃላትን ሲሰነዝሩ እና ለትዝብት ሲዳረጉ ተመልክተናል። በዚህ ረገድ ሊመሰገኑ የሚገባቸው የሲዳማ ቡና ደጋፉዎች ግን “ጎል አማረን ውጤት አማረን” በማለት ሲያዜሙ የተሰሙ ከመሆኑ ውጪ ሽንፈቱ የፈጠረባቸውን ህመም ቻል አድርገውት ጨዋታውን ጨርሰዋል። ከዚህ ባለፈ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ አራተኛ ሽንፈት ያገኛቸው አዲሱ አሰልጣኛቸው ገብረመድህን ኃይሌን በማበረታት ከስታድየሙ ወጥተዋል።

👉 የአራተኛ ዳኛው መቀየር

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከተደረጉ ጨዋታዎች ውስጥ በሁለተኛው ቀን ማለዳ የተደረገው የሀዲያ ሆስዕና እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ አንዱ ነው። በዚህ ጨዋታ የተደረገው የዳኞች ለውጥ በወቅቱ አነጋጋሪ ሆኖ ታይቷል። በጨዋታው በአራተኛ ዳኝነት ተመድበው የነበሩት ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው በሜዳ ላይ ከተገኙ በኋላ በፌደራል ዳኛ ዮናስ ካሳሁን የተተኩበት አኳኋን ያልተለመደ ነበር። በክስተቱም በመጨረሻ ደቂቃዎች ከኃላፊነት የተነሱት ኢንተርናሽናል አርቢት በውሳኔው ደስተኛ ያልነበሩ መሆኑን መታዘብ ችለናል። ከዚህ ጋር ባይገናኝም በአጠቃላዩ የዳኞች ምደባ ላይም በጭምጭምታ የሚሰሙ ቅሬታዎች አሉ። በተደጋጋሚ የማጫወት ዕድል የሚሰጣቸው ዳኞች እንዳሉ ሁሉ ለረጅም ጊዜ ከዕይታ የሚርቁ ዳኞች መኖራቸው ቅሬታዎችን እንዳስነሳም ይሰማል። በቴሌቪዢን ስርጭት ሽፋን ምክንያት ዳኝነት ራሱ በተደጋጋሚ ለዳኝነት እየቀረበበት ባለበት በአሁኑ ወቅት መሰል ጉዳዮች ተጨማሪ ችግር ይዘው ሊመጡ ስለሚችሉ በቶሎ መፍትሄ መስጠት ከሚመለከተው አካል ይጠበቃል።

👉 በመጨረሻም ያፈሰሰው መረብ

የባህር ዳር ኢንተርናሽናል ስታድየም ከመጫወቻ ሜዳ አንስቶ በአጠቃላይ የውስጥ ግንባታው እና የቅጥር ግቢው ጭምር ሲወደስ ከርሟል። በተለይም የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታዎች በጀመሩባቸው ቀናት ይበልጥ ትኩረትን ስቦ ቆይቷል። በከፍተኛ ጫና በርካታ ጨዋታዎችን ያለ በቂ ዕረፍት በማስተናገዱ ግን እየፈተነው መሄዱ አልቀረም። እጅግ ውብ የሆነው የመጫወቻ ሜዳው በተወሰኑ ክፍሎቹ ላይ ወደ መድረቁ ሲሄድ የተመለከትን ሲሆን በመጨረሻው ሳምንት ላይ ደግሞ ሌላ ክስተትን አስመልክቶናል።

አዳማ ከተማ እና ባህር ዳር ከተማን ባገናኘው ጨዋታ ብቸኛዋ የፍፁም ዓለሙ ጎል ስትቆጠር ኳሷ በመረቡ ሾልካ መውጣቷ አነጋጋሪ ነበር። በወቅቱ ፍፁም እና ጓደኞቹ ግቧ ስለመቆጠሯ እርግጠኛ ሆነው ደስታቸውን ሲገልፁ በአንዳንድ የአዳማ ተጨዋቾች እና በተመልካቹም ዘንድ መደናገር ተፈጥሮ ተመልክተናል። ከጨዋታ መጀመር አስቀድሞ የዕለቱ አርቢትሮች ፍተሻ ሲያደርጉ መረቡ መቀደዱን አለማረጋገጣቸው አንድ ነገር ሆኖ ግዙፉ ስታድየም በቅርቡ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታን እንደማስተናገዱም ጥቃቅን ከሚመስሉ ተመሳሳይ ችግሮች ነፃ ሆኖ እንዲገኝ ይጠበቃል።

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ከሳምንታት በፊት ከሊግ ካምፓኒው አስተባባሪዎች ጋር በነበረን ቆይታ እንደሀገር የግብ መረቦችን ከውጪ ማስመጣት ላይ ክፍተት እንዳለ ሰምተናል። በሀገር ውስጥ የሚመረቱት መረቦች ደግሞ የጥራት ደረጃቻው በሚፈለገው መጠን ሲገኝ አይስተዋልም። በዚህ አጋጣሚም ለችግሩ መፍትሄ ያለው አካል ከፌዴሬሽን እና ከሊግ ካምፓኒው ጋር ቀርቦ ለመስራት ቢሞክር መልካም ነው እንላለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ