የአስራ ሰባተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ጨዋታ ዛሬ ረፋድ በአንድ ጨዋታ ሲጀመር አርባምንጭ ከተማ እና ጌዲኦ ዲላ ያለ ጎል ጨርሰዋል፡፡
ለዕይታ ብዙም ሳቢ ባልነበረው የመጀመሪያው አጋማሽ መሐል ሜዳ ላይ ብቻ የተገደበ እንቅስቃሴ ሲታይበት በአንፃራዊነት የቀኝ የሜዳውን ክፍል ለመጠቀም በተደጋጋሚ ሲሞክሩ የተስተዋሉት አርባምንጮች በተወሰነ ረገድ የግብ አጋጣሚን ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ለማግኘት ሲታትሩ ታይቷል፡፡ በዚህ የጨዋታ መንገዳቸው 23ኛው ደቂቃ ላይ በድርሻዬ መንዛ አማካኝነት ግብ ቢያስቆጥሩም ከጨዋታ ውጪ ተብሎባቸዋል፡፡
አብዛኛዎቹን ደቂቃዎች መሀል ሜዳ ላይ ያሳለፉበት ጌዲኦ ዲላዎች ከዚህ ቀደም ይንፀባረቅባቸው የነበረው ትጋት ዛሬ አብሯቸው አለመኖሩ ወደ ግብ ለመድረስ የነበራቸው ተሳትፎ እጅጉን ቀዝቃዛ ነበር፡፡ ከቆመ ኳስ ቤተልሄም አስረሳኸኝ 41ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት በቀጥታ መታ ድንቡሽ አባ የተቆጣጠረችባት ኳስ ክለቡ ያደረጋት ብቻ የጠራች አጋጣሚ ነበረች፡፡
ከመጀመሪያው አጋማሽ በባሰ ተዳክሞ የቀጠለው ሁለተኛው አጋማሽ ከእንቅስቃሴ አንፃር ተመጣጣኝ የሚባል ጊዜን ቡድኖቹ ማሳለፍ የቻሉ ሲሆን ወደ ጎል ደርሶ ልዩነት ለመፍጠር ሲያደርጉት የነበረው ጥረት ግን እምብዛም ነበር፡፡59ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃተ ይታገሱ ተገኝወርቅ በቀኝ በኩል ያገኘችሁን ኳስ በፍጥነት ወደ ግብ ክልል ስታሻማ ቱሪስት ለማ አግኝታው ወደ ጎል ብትመታው ግብ ጠባቂዋ ድንቡሽ የመለሰችባት ምናልባት ጌዲኦ ዲላን መሪ ለማድረግ የሰፋ ዕድል የነበራት ብትሆንም ወደ ጎልነት ሳትለወጥ ቀርታለች፡፡
በአሰልቺነቱ የዘለቀው ቀሪው የቡድኖቹ ጨዋታ ኳስን ሜዳ ለማንሸራሸር ከሚደረጉ ሁነቶች ውጪ ሊጠቀሱ የሚችሉ ሙከራዎችን ሳንመለከት ያለ ጎል 0ለ0 ተጠናቋል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ