የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ውድድር ሊጠናቀቅ የአንድ ሳምንት የጨዋታ ዕድሜ ብቻ እየቀረው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውድድሩ አሸናፊ መሆኑን አረጋግጧል። ባንክን ከ2004 ጀምሮ እያሰለጠኑ የሚገኙት አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛውም የሊግ ድሉን ማሳካታቸውን ካረጋገጡበት የዛሬው ጨዋታ በኃላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ስለ ድሉ፣ ስለ ቻምፒዮንነቱ እና ስለ ውድድር ዘመኑ ጉዞ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ስለ ቻምፒዮንነታቸው
“ከመጀመሪያም ጀምሮ ሁለት ሦስት ጨዋታዎች ሲቀረን ቻምፒዮን እንደምንሆን ዕርግጠኛ ነበርኩ። ምክንያቱ ደግሞ ተጫዋቾቼ ላይ የሚነበበው ነገር ነው። ትላልቅ ተጫዋች መያዝ ጥሩ ነገሩ ለምንም ነገር በራ መተማመን ይሰጥሀል። በምታሰራቸው ጊዜ ችግሮችንም በምታይበት ጊዜ ቶሎ የመንቃት ባህሪ አላቸው። እኔም ደግሞ በዚህ ዕድለኛ ነኝ። ተጫዋቾቼ እኔ በፈለግኩት መሠረት ሄደውልኛል።”
ስለዛሬው ጨዋታ
“በዛሬው ጨዋታ አንድ ለዜሮ እየተመራን ተቃራኒ ቡድን ላይ ከፍተኛ ብልጫ ወስደናል። እንደምናገባ ዕርግጠኛ ነበርኩ። ሰዓት እያለቀ ሲሄድ ተጫዋቾቼ ተስፋ እንዳይቆርጡ ነግሬያቸው ነበር፡፡ የዛሬ ቀን ደስተኛ የሆንኩበት ነው፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላ ዋንጫውን በማግኝታችን ፈጣሪዬን አመስግነዋለሁ፡፡ ሁሌም በፀሎቶቼ የማትለየኝን ድንግል ማርያምን አመሰግናታለሁ።”
ስለ ፎዚያ ቅያሪ
“ፎዚያን ቀይሬ ሳስገባት አስቤበት ነው። ከዚህ በፊትም ተቀይራ ገብታ ሁለት ጎል አመቻችታ ሁለት ጎል ያገባች ነበረች። ታዳጊ፣ ፈጣን፣ ለነገ ትልቅ ህልም ያላት፣ ንግድ ባንክንም ወደ ፊት በደንብ የምታገለግል ተጫዋች ስለሆነች እሷ ከገባች አንድ ነገርን እንደምናገኝ ተስፋ በማድረግ ነው ምክትል አሰልጣኜን በአስቸኳይ ቀይርልኝ ያልኩት። የሌሎቹ ዕገዛ ቢኖርም ፎዚያ በደንብ ጨዋታውን ቀይራዋለች። ለዚህች ታዳጊም ክብር አለኝ።”
ስለ ውድድር ዓመቱ
“ይህ ዓመት ጫና የነበረበት ነበር። አንደኛው ጫና ዝግጅት በጊዜ አለመጀመራችን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ኮቪድ በጣም አስቸግሮን ነበር። ሌላው ደግሞ ከውድድሩ ፈታኝነት አንፃር ስኳዳችን ሰፊ አልነበረም። ጥራት ያላቸው ተጫዋቾች አሉኝ እንጂ ሙሉ ሀያ አምስት ተጫዋቾች የሉኝም። ይሄ ይሄ ነገር ፈትኖኛል። ተጫዋቾችም በተደጋጋሚ ተጎድተውብኛል። እንዲህም ሆነን ቻምፒዮን በመሆናችን በጣም በጣም ደስ ብሎኛል።”
በሁለተኛው ዙር ስለመዳከማቸው
” የመጀመሪያ ምክንያት በተጫዋቾች ላይ የነበረው ተደጋጋሚ ጉዳት በሀዋሳ የነበረንን የበላይነት እንዳናሳይ እክል ፈጥሮብናል። እዛ የተጠቀምናቸውን በአብዛኛዎቹን ልናገኝ አልቻልንም። ሁለተኛ ደግሞ ከአንደኛው ዙር በጣም ከባዱ ይሄ ዙር ስለሆነ በጣም ተቀራራቢ አቋም እና ውጥረት የነበረበት ነው። ዘጠኙም ክለቦች ለንግድ ባንክ ብለው ተዘጋጅተው መምጣታቸው እንዲከብደን አድርጓል።
© ሶከር ኢትዮጵያ