ከአንድ ሀገር ውጪ ሀያ ሦስት ተሳታፊ ሀገራትን የለየው የካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ድልድሉ የሚያደርግበት ቀን ታውቋል።
በኮሮና ቫይረስ ከ2021 ወደ 2022 የተዘዋወረው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ የአህጉሪቱ ብሔራዊ ቡድኖች በአስራ ሁለት ምድብ ተከፋፍለው የምድብ የማጣሪያ ጨዋታቸውን ሲያደርጉ ከርመዋል። እስካሁንም የውድድሩ አዘጋጅ ካሜሩንን ጨምሮ ሀያ ሦስት ቡድኖች በውድድሩ ላይ የሚያሳትፋቸውን ማረጋገጫ አግኝተዋል። በውዝግቦች የተሞላው የቤኒን እና ሴራሊዮን ጨዋታ ግን እሳካሁን የለየለት ውሳኔ አላገኘም።
አይቮሪኮስትን ተከትለው ወደ አህጉሪቱ ትልቁ የሀገራት ውድድር ያለፉት ዋልያዎቹን ተሳታፊ የሚያደርገው ውድድርም ከጥር 1 2014 እስከ ጥር 29 ድረስ እንደሚካሄድ ተገልጿል። የውድድሩ የእጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት ደግሞ ሰኔ 18 እንደሚደረግ ታውቋል።
ለ33ኛ ጊዜ በሚደረገው ውድድር ላይ ካሜሩን (አዘጋጅ)፣ ሴኔጋል፣ ቱኒዚያ፣ አልጄርያ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ፣ ጊኒ፣ ኮሞሮስ፣ ጋምቢያ፣ ጋቦን፣ ግብፅ፣ ጋና፣ ኢኳቶርያል ጊኒ፣ ዚምባብዌ፣ ሞሮኮ፣ አይቮሪኮስት፣ ናይጄርያ፣ ሱዳን፣ ማላዊ፣ ኢትዮጵያ፣ ሞሪታንያ፣ ጊኒ ቢሳው እና ኬፕ ቨርድ መሳተፋቸውን ያረጋገጡ ሀገራት እንደሆኑ ይታወቃል።
© ሶከር ኢትዮጵያ