ዋልያዎቹ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አቀባበል ይደረግላቸዋል

ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው የተመለሱት ዋልያዎቹ በነገው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አቀባበል ሊደረግላቸው መሆኑ ተሰምቷል።

በካሜሩን አስተናጋጅነት ለሚደረገው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ መሳተፉን ያረጋገጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ትናንት ምሽት አዲስ አበባ ከደረሰ በኋላ በተለያዩ አካላት ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል። ልዑካኑ በዛሬው ዕለትም በአዲስ አበባ የተለያዩ ጎዳናዎች ላይ እየዞረ ከአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ደስታውን ሲገልፅ ውሏል።

አሁን በተሰማ መረጃ መሠረት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወደ አፍሪካ ዋንጫ የተመለሰውን ቡድን በይፋ ለመቀበል ነገ ቀጠሮ ይዟል። በዚህም ቡድኑ በከተማ መስተዳደሩ ነገ ማለዳ 1 ሰዓት በወዳጅነት ፓርክ ደማቅ አቀባበል ይደረግለታል። በቦታውም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ እና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች እንደሚገኙ ሰምተናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ