የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ የሆነው አቡበከር ናስር በቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች ስጦታ ተበርክቶለታል።
የዘንድሮ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነትን እየመራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቡናው አጥቂ አቡበከር ናስር በሊጉ አልፎም በብሔራዊ ቡድኑ እያሳየ ባለው ብቃት በርካታ አድናቆቶችን እያገኘ ይገኛል። ከወራት በፊትም የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ የነበረው ዮርዳኖስ ዓባይ የተጫዋቹን ብቃት አድንቆ የማበረታች እና የአድናቆት መልዕክት ማስተላለፉ ይታወሳል። ዛሬ ደግሞ በኢትዮጵያ መድህን የእግር ኳስ ህይወቱን ጀምሮ በኢትዮጵያ ቡና፣ መከላከያ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ወልዋሎ ዓ/ዩ የቀጠለው ሙሉዓለም ጥላሁን ለተጫዋቹ የማበረታቻ ሽልማት አበርክቶለታል።
በአሁኑ ሰዓት በጀርመን የሚገኘው ሙሉዓለም ተጫዋቹ በዘንድሮ የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ባሳየው አቋም በትዕዛዝ ለአምስት ሳምንታት የቆየ እና ስሙ ከሚለብሰው ቁጥር ጋር የተፃበፈት የመጫወቻ ጫማ አዲስ አበባ በምትገኘው ተወካዩ ፀጋ ጥላሁን (እህቱ) አማካኝነት አበርክቶለታል። ከታኬታው በተጨማሪም በተለያዩ ቀለሞች የተመረቱ የመጫዎቻ ታይቶች እና የስፖርት ቦርሳዎች ለተጫዋቹ ተሰጥቷል።
አመሻሽ አስር ሰዓት በተከናወነው ፕሮግራም አቡበከር ስጦታዎቹን ከተቀበለ በኋላ ደስተኛ መሆኑን ገልፆ ለመጀመሪያ ጊዜ በቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች ለተበረከተለት ስጦታ ምስጋና አቅርቧል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በተለያዩ የእድሜ እርከኖች የወከለው እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና 2003 የሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ ቁልፍ ተጫዋች የነበረው ሙላለም ጥላሁንም ከዚህም በኋላ በኢትዮጵያ እየወጡ ላሉ ወጣት ተጫዋቾች የማበረቻቻ ሽልማት ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን እና ሌሎች የቀድሞ ተጫዋቾችም ይህንን አይነት ተግባር እንዲፈፅሙ እያስተባበረ መሆኑን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል።
© ሶከር ኢትዮጵያ