” አንድነት፣ ፍላጎት፣ መተሳሰብ እና ተነሳሽነት የቡድናችን ጥንካሬ ነበር” – አቡበከር ወንድሙ (አዲስ አበባ ከተማ)

አቡበከር ወንድሙ ይባላል። ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ፉሪ አካባቢ ነው። በታዳጊነቱ ከትምህርት ቤት ውድድር ጅማሮውን ያደረገው የእግርኳስ ህይወቱ በማስከተል በክለብ ደረጃ ለቅዱስ ጊዮርጊስ መጫወት የቻለው አቡበከር በማስቀጠል ለአራዳ ክ/ከተማ፣ ከፋ ቡና እና ሀላባ ከተማ ሲጫወት ቆይቶ ዘንድሮ በአሰልጣኝ እስማኤል አቡበከር ምርጫ አዲስ አበባን ተቀላቅሏል። 

አዲስ አበባ ወደ ፕሪምየር ሊግ ዳግም እንዲመለስ ካስቻሉ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች መካከል ሰባት ጎሎችን በማስቆጠር በርከት ላሉ ጎሎች መቆጠር አመቻችቶ በማቀበል በአመዛኙ ጨዋታ ላይ መሳተፍ የቻለው የመስመር አጥቂው አቡበከር ሚና ከፍተኛ ነበር። ከነበረው አስተዋፆኦ በመነሳት በተገኘው ውጤት ዙርያ እና በቀጣይ ስለሚያስበው ህልሙ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።

” ዘንድሮ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንመለሳለን ብለን በእርግጥ እንደዚህ አላሰብንም። ቡድኑ ከያዘው ዕቅድ አንፃር መቆየትን ያሰበ ይመሰለኛል። ሆኖም ጥሩ ልጆች በቡድኑ መቀላቀላቸው፣ ጥሩ ቅንጅት እና ዓላማ የነበረን በመሆኑ የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ አዲስ አበባን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ልንመልሰው ችለናል።

” ጎል ካስቆጠርኩት ይልቅ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ያመቻቸሁት ይበልጣል። ያው የመስመር አጥቂ እንደመሆኔ መጠን የተሻሉ ኳሶችን ዕይታ በሚፈቅደው መጠን ለአጥቂዎች በማቀበል ያስፈልጋል። በዚሁ አጋጣሚ ጎል ማስቆጠር የሚቻል ከሆነ ማግባት ይገባል። ያው እግርኳስ ተጫዋች እስከሆንክ ድረስ በሁለቱም ላይ መሳተፍ ግዴታ ነው።

” ወደ አዲስ አበባ ለመግባት ስመጣ በሙከራ አበበ ቢቂላ ሜዳ በተደረገ ምርጫ ነው የተያዝነው። ሀላባ እያለሁ ትንሽ ትከሻዬ አካባቢ አሞኝ ነበር። በዚህም ግማሽ ዓመት ሳልጫወት ቀርቼ ነበር። ክረምት ላይ ያለ እረፍት ነበር ስሰራ የነበረው። በዚህም ሙከራው ላይ ባሳየሁት ነገር ዕይታ ውስጥ ገብቼ አዲስ አበባ ልገባ ችያለው። አሰልጣኝ እስማኤል እንደ ትልቅ አሰልጣኝ ብዙ ነገር አስተምሮናል። ነፃ ሆነን ጥሩ ኳስ እንድንጫወት በመፍቀድ ውጤታማ አድርጎናል።

” ከሁሉም ነገር በላይ እንደ ቡድን አንድ መሆናችን፣ ፍላጎት፣ መተሳሰብ፣ ተነሳሽነትነታችን የቡድናችን ጥንካሬ ነበር። ይህ ነው የተሻለ ነገር እንድንሰራ ውጤታማ ያደረገን። በሜዳ ላይም በእያንዳንዱ ጨዋታ ትኩረት ሰጥተን መጫወታችን ውጤታማ አድርጎናል።

“ጥሩ የሚባል የውድድር ጊዜ ዘንድሮ አሳልፌያለው። ከዚህ በኃላም እራሴን በማሳደግ በብሔራዊ ቡድን ሀገሬን ለመጥቀም ነው የማስበው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ