በፋሲል አሸናፊነት ከተጠናቀቀው የከሰዓቱ ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች ቀጣዩን ሀሳብ ለሱፐር ስፖርት አካፍላዋል።
አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ
ስለጨዋታው
በመጀመሪያው አጋማሽ ሲዳማ ፈትኖናል ፤ የእኛም ጥሩ ነው። ሁለተኛው አጋማሽ ግን የእኛ ቡድን በጣም ጥሩ ነበር። የነበረን ጫና ፣ ጎሎች ለማግኘት ስናደርግ የነበረው ጥረት እንዲሁም ተጋጣሚያችን የበለጠ ክፍተት እንዳያገኝ እያደረግን የነበረው ጥሩ ነበር። እንዲያም ሆኖ እነሱ ካስቆጠሩ በኋላ ደግሞ ሙሉ ነጥብ መውሰድ ስለነበር የምንፈልገው አጥቂ መጨመር ፈለግን ፤ ያንን አድርገን ውጤታማ መሆን ችለናል። በሁለታችንም በኩል ጥሩ ፉክክር ነበር ፤ በሁለተኛው አጋማሽ ግን የእኛ ቡድን ደህና ነበር ብዬ አስባለሁ።
ስለሙጂብ እና ፍቃዱ ጥምረት
በጣም ጥሩ ነው። ነጋር ግን ይህ ጥምረት ሊመጣ የሚችለው አማካዩ ጠንካራ ሲሆን ነው። ምክንያቱም ከፊት ሁለት አጥቂ ስትጠቀም መሀል ላይ ጥሩ የሆኑ ቡድኖች ብልጫ ሊወስዱብህ ይችላሉ ፤ ለዛም ነው አማካይ ስናበዛ የነበራው። ነገር ግን ፍቃዱ በራሱ የራሱ ጥንካሬ አለው ፤ የጊዜ ጉዳይ ነው። ያደረግነው ለውጥ ጠቅሞናል። በተለይ በጣም የምንፈልገው ነጥብ ነው እና ይህን ማግኘታችን ለጉዟችን ትልቅ አስተዋፅዖ ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ።
ውጤቱ ለቀጣዩ ጉዟቸው ስላለው አስተዋፅዖ
ያሁኑ ብቻ ሳይሆን ከባህር ዳር ጋር ነጥብ መጋራታችንም ትልቅ ውጤት ነው። ይሄ ነጥብ ግን ለእኛ በጣም ጥሩ ነው። ምክንያቱም ተከታዮቻችን እርስ በእርስ የሚያደርጉት ከፍተኛ ፉክክር ስላለ በዛ መካከል ሾለክ ለማለት ዕድሉ አለን። ቀሪ ሁለት ጨዋታዎቻችንን በዚህ ትጋት መጨረስ አለብን። ከዛ በኋላ የሀዋሳውን ጨዋታ ማሟያ እናረገዋለን። ወጣቶቻችንን ለማየት የምንችልበት እናደርገዋለን። ከሁሉም በላይ እዚህ ድረስ ታግሶን ከፍተኛ ደጋፍ ያደረገልን የፋሲል ከነማን ደጋፊ በዚህ አጋጣሚ እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለሁ።
አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ – ሲዳማ ቡና
የአጨራረስ ችግር ዋጋ ያስከፈላቸው ስለመሆኑ
አዎ በትክክል አስከፍሎናል። በተለይ መጨተሻ አካባቢ በሀብታሙ ኳስ መግደል እንችል ነበር ፤ ግን ሀብታሙ ጥሩ ጥረት አድርጓል። ከዛ ውጪ አጠቃላይ ቡድኑ ያደረገው ጥረት እና አልሸነፍ ባይነቱ ሊመሰገን የሚገባው ነው። መሸናነፍ ያለ ነው። ይሄ አይገርመንም ፤ የሚመራ ቡድን ነው። ፋሲል በደረጃም በምንም ጥሩ ነው። ነገር ግን ዛሬ በጥሩ ሁኔታ ተዘጋጅተን ቀርበናል። ማሸነፍ ግን አልቻልንም ፤ ለማሸነፍ ነበር የገባነው።
ስለጨዋታ ዕቅዳቸው
ጨዋታው በአጠቃላይ ፈታኝ ነው። በአንድ ታክቲክ ላይ ተመስርተህ በመዘጋጀት የሚሆን አይደለም። ሜዳው ጭቃማ ነው ፤ ፈታኝ ነው። ስለዚህ ሁኔታ ጥረት እና ፍላጎት ይጠይቃል። መሸነፉ አንድ ነገር ሆኖ በብቃት ደረጃ ግን ጥሩ ነበር።
መጨረሻ ላይ ቡድኑ የጉልበት ማነስ ስለማሳየቱ
የማነስ አይመስለኝም። አንዳንድ ውሳኔዎች ላይ ትንሽ የሚያቀዘቅዙ ነገሮች ነበሩ። በዳኛ ማሳበብ ባይገባም። ግን ሰው ላይ ተደግፎ ነው ያገባው ልጁ ፤ እሱ ደግሞ ትክክል አይደለም። ነገር ግን እነዚህ ዓይነት ነገሮች ያወርዳሉ። ከዛ በፊትም በቀይ መውጣት የሚገባው ተጫዋችም ነበር ፤ በሁለተኛ ቢጫ። ቢሆንም እሱ ላይ ትኩረት አናዳርግም። በአጠቃላይ በነበረው ጨዋታ በጣም ደስተኛ ነኝ።
© ሶከር ኢትዮጵያ