ቅድመ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

በ20ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቸን ነጥቦች አንስተናል።

ባሳለፍነው ሳምንት ቀላል ከማይባሉ ተጋጣሚዎቻቸው ሙሉ ነጥብ ማግኘት የቻሉት ሁለቱ ቡድኖች ነገ እርስ በእርስ ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርጉ በሚጠበቁበት ጨዋታ ይገናኛሉ። ከሲዳማ ቡና ጋር ነጥብ ለመጋራት ተቃርበው የነበሩት ፋሲል ከነማዎች በመጨረሻ ደቂቃ አሸንፈው በአንደኝነታቸው ሲደላደሉ ሀዲያ ሆስዕናም ጠንቃቃ የነበረው ወልቂጤ ከተማን 2-0 ባማሸነፍ የደረጃ ፉክክሩን ገፍቶበታል። በቶሎ የቤት ሥራቸውን ማጠናቀቅ የሚፈልጉት አፄዎቹም ሆኑ የኮንፌደሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ ዕድል በእጃቸው ያለው ነብሮቹ ነገ በቀላሉ የሚላቀቁ አይመስልም።

በጨዋታው ፋሲል ከነማ በተለመደው የማጥቃት አቀራረቡ ጨዋታውን እንደሚጀምር ሲገመት ሀዲያ ሆሳዕና ጥንቃቄ አዘል የጨዋታ ዕቅድ ሊኖረው ይችላል። ሁለቱም ቡድኖች በዚህ አኳኋን ጨዋታውን ለማድረግ የሚያስችል ያለፈ ጨዋታ ታሪክ ያላቸውም ይመስላል። ፋሲል ከነማ በተወሰኑ ቅፅበቶች ብልጫ ተወስዶበት ራሱን ለመከላከል ጥረት ሊያደርግ ይችላል እንጂ በአመዛኙ ኳስን ተቆጣጥሮ በፈጣን አኳኋን ወደ ፊት ለመሄድ ሲጥር ይታያል። በተቸገረባቸውም ጨዋታዎች ስትራቴጂዎችን በመቀየር እስከመጨረሻው መፋለም እና ውጤት የማግኘት ባህሪው በቅርብ ጨዋታዎች ታይቷል። በሊጉ ዝቅተኛ ግብ ያስተናገደው ሀዲያ ሆሳዕና በበከሉ በጥንቃቄ እንደማይታማ ቁጥሮች በራሳቸው ምስክር ናቸው። እስካሁን በአመዛኙ ከኳስ ጋር ብልጫ ሊወስዱበት የሚችሉ ተጋጣሚዎችንም በዚሁ አኳኋን ፈትኖ ውጤት ሲያሳካ በተደጋጋሚ ታይቷል።

ጠንከር ያለ የአካል ብቃት ፍልሚያም ሌላው የጨዋታው ባህሪ መሆኑ የሚቀር አይመስልም። አማካይ ክፍል ላይ ያለው የነብሮቹ ክፍተቶችን የመዝጋት ጥንካሬ ከፋሲል ከነማ አብሮ የቆየ የመሀል ሜዳ ተሰላፊዎች የማጥቃት ዑደት ጋር ሲፈናኝ ፍትጊያው ሊጨምር ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ የሁለቱም ቡድኖች የፊት መስመር ተሰላፊዎች ፈጣን መሆን በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት ለተከላካይ መስመሮቹ የሚሰጠው ፈተና እና የእነርሱም ምላሽ በራሱ ፍልሚያውን ከፍ የሚያደርግ ነው። በመጨረሻ ጨዋታዎቻቸው ላይ የታዩት ከቆሙ እና ከተሻጋሪ ኳሶች መነሻቸው ያደረጉ ጎሎች ደግሞ በእንቅስቃሴ የምንጠብቀውን ፍትጊያ በእነዚህ ቅፅበቶች ወቅትም ትኩረታችንን እንዲስቡ የሚያደርግ ነው።

በ19ኛው ሳምንት የተደረጉት ጨዋታዎች ከተነሱ አይቀር ሁለቱም በየፊናቸው ሙሉ ውጤት ለማሳካት እስከ ፍፃሜው የታተሩበት መንገድ ለነገው ጨዋታም ምልክት የሚሰጥ ነው። ከሁለት ተጋጣምሚዎች መሰል የጨዋታ ፍላጎት እና አይደክሜነት የሚታይ ከሆነ ደግሞ ሰሞንኛውን በጠንካራ ፉክክር የታጀቡ ዘጠና ደቂቃዎች ነገም ደግመን እንድናይ ተስፋ የሚሰጥ ነው። ከዚህ አንፃር ቀድሞ ግብ የሚያስቆጥር ቡድን ጨዋታውን በራሱ መንገድ የማስኬድ ዕድሉ የሰፋ ይሆናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ዘንድሮ የተመዘገበው የመጀመሪያ የሊግ ግንኙነታቸው ፋሲል ከነማ የሙጂብ ቃሲም ጎል አሸናፊ ሆኗል።

* ወቅታዊው የኮቪድ ወረርሺኝ በቡድኖቹ የስብስብ ምርጫ ላይ እያሳደረ ካለው ተለዋዋጭነት አንፃር ግምታዊ አሰላለፍ ለማውጣት አዳጋች በመሆኑ የወትሮው የአሰላለፍ ትንበያችን በዳሰሳው ያልተካተተ መሆኑን እንገልፃለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ