ሪፖርት | ሆሳዕና እና ድሬዳዋ ያለ ጎል አቻ ተለያይተዋል

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሃያ አንደኛ ሳምንት በሁለተኛ ደረጃ ፉክክር እና ባለመውረድ ትንቅንቅ ውስጥ የሚገኙት ሆሳዕና እና ድሬዳዋን ያገናኘው ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከፋሲል ነጥብ ከተጋራበት ስብስብ የአምስት ተጫዋች ለውጥ በማድረግ በሱሌይማን ሀሚድ፣ ቴዎድሮስ በቀለ፣ ሄኖክ አርፊጮ፣ ካሉሻ አልሀሰን እና ቢስማርክ አፒያ ምትክ አይዛክ ኢሲንዴ፣ ብሩክ ቀልቦሬ፣ ዱላ ሙላቱ፣ ተስፋዬ በቀለ እና ተስፋዬ አለባቸውን ሲያሰልፍ ድሬዳዋ ከተማዎች በበኩላቸው የአንድ ተጫዋች ለውጥ ብቻ በማድረግ በሙኅዲን ሙሳ ምትክ ኢታሙና ኬሙይኔን በአሰላለፉ አካተዋል።

የከተማው ፖሊስ ማርሽ ባንድ ታጅቦ በተጀመረው ጨዋታ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ተገኝተው ጨዋታውን የተከታተሉ ሲሆን ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ ንግግር በማድረግ ለሊግ ኩባንያው እና ለሱፐር ስፖርት የማስታወሻ ስጦታ አበርክተዋል።

በዕለቱ በጣለው ዝናብ እና ቀደም ብሎ በተካሄደው ጨዋታ ምክንያት ሜዳው ጨቅይቶ ለእንቅስቃሴ አስቸጋሪ የነበረ ሲሆን በጨዋታው የተደራጀ የማጥቃት እንቅስቃሴም ሆነ የተሳካ ቅብብል ለማድረግ አስቸጋሪ ሆኖ ታይቷል።
በቀጥተኛ ኳሶች ቶሎ ቶሎ ወደ ሆሳዕና የጎል ክልል ለመድረስ የሞከሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ የጎል ዕድሎች መፍጠር ችለው ነበር። ሆኖም ናሚቢያዊው አጥቂ ጁንያስ ናንጄቦ ላይ ብቻ የተመሰረተው የማጥቃት እንቅስቃሴ ይበልጥ አደጋ መፍጠር እንዳይችሉ አግዷቸዋል። በዚህም ናንጄቦ ከቀኝ መስመር የተላከውን ኳስ አመቻችቶ በግራ እግሩ መትቶ ግብ ጠባቂው የያዘበት፣ ከቀኝ እና ከግራ የሳጥኑ ክፍል አክርሮ መትቶ ኢላማውን ሳይጠብቅ ወደ ውጪ የወጡበት ሙከራዎችን አድርጓል።

በሦስት የተከላካይ አማካዮች የተዋቀረ ቡድን ይዘው የቀረቡት ሀዲያ ሆሳዕናዎች የሚጠቀስ ጥቃት ለመሰንዘር ተቸግረው ሲታዩ ከሁለት ቀናች በፊት ከፋሲል ከነማ ጋር ካደረጉት ፈታኝ ጨዋታ በሚገባ እንዳላገገሙ በሚያሳይ መልኩ እንቅስቃሴያቸው ተዳክሞ ታይቷል። ይልቁንም በሁለት አጋጣሚዎች ዳዋ ሆቴሳ ያገኛቸውን መልካም አጋጣሚዎች ሳይጠቀምባቸው በጥሩ ብቃት ላይ የሚገኘው ፍሬዘር ካሣ በድንቅ ሁኔታ ያገዳቸው በአጋማሹ ትኩረት የሳቡ ክስተቶች ነበሩ።

ከመጀመርያው በእጅጉ የቀዘቀዘ እና ይበልጥ የሜዳው ጭቃማነት አይሎ ለጨዋታ አስቸጋሪ መልክ የያዘበት ሁለተኛው አጋማሽ አንድ የጠራ የግብ እድል ብቻ የተፈጠረበት ሆኖ አልፏል። በ61ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ጁንያስ ናንጄቦ በግንባሩ ገጭቶ ሙንታሪ በጥሩ ቅልጥፍና ያወጣበት ድሬዳዋን ምናልባትም መሪ ልታደርግ የተቃረበች ሙከራ ነበረች።

በሁለተኛው አጋማሽ በ62ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው አልሀሰን ካሉሻ በ84ኛው ደቂቃ ተመልሶ ተቀይሮ ከወጣበት ክስተት በቀር ሌላ የተለየ ክስተት ሳንመለከት ጨዋታው ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ሀዲያ ሆሳዕና ወደ ሁለተኛ ከፍ የማለት ዕድሉን ሲያመክን ድሬዴዋ ከተማም በነበረበት አስረኛ ደረጃ ላይ ረግቷል።



© ሶከር ኢትዮጵያ