የአዲስ አበባ ከ17 ዓመት በታች የማጠቃለያ ውድድር በአዳማ ከተማ አሸናፊነት ተፈፅሟል

በአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስተናጋጅነት ላለፉት ወራት በ13 ቡድኖች መካከል ሲካሄድ የሰነበተው ከ17 ዓመት በታች ውድድር በአዳማ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።

አንጋፋው የእግርኳስ ሰው እና ጊዜያዊው የአዲስ አበባ እግርኳስ የፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አሥራት ኃይሌ፣ ምክትል ፕሬዝደንት ደረጄ አረጋ እና ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ በታደሙት የፍፃሜ ጨዋታ አስቀድሞ ሦስቱን የመጨረሻ ጨዋታዎችን በወጣው መርሐግብር መሰረት በዕኩል ሰዓት በተለያየ ሜዳ ለማድረግ ታስቦ የነበረ ቢሆንም አወዳዳሪው አካል በአንድ ቦታ በተለያየ ሰዓት ለማድረግ ባወጣው የፕሮግራም ለውጥ ምክንያት ጠዋት ሦስት ሰዓት የመጀመርያው ጨዋታ ተደርጓል።

በቅድሚያ ዲኤፍቲን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ያገናኘው ጨዋታ ሦስት አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል። በመጀመርያው አጋማሽ እንደወሰዱት ብልጫ ጎል ማስቆጠር የሚገባቸው ኤልፓዎች በዕለቱ ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያስመለክተን የዋለው ፍቃዱ ለማ የራሱን የግል ጥረት ተጠቅሞ ሁለት ግሩም ጎሎችን አከታትሎ አስቆጥሮ ኤልፓዎችን ሁለት ለዜሮ እንዲመሩ አስችሏቸዋል። የመስመር አጥቂው ጎሉን ካስቆጠረ በኃላ ለአሳዳጊ ክለቡ ዲፍቲ ያለውን አክብሮት ደስታውን ባለመግለፅ አሳይቷል።

በዚህ ውድድር ከተሳተፉ ቡድኖች መካከል የግል ቡድን በመሆን የቀረበው በአሰልጣኝ ቶፊቅ ከማል የሚመራው ዲኤፍቲ የዘንድሮ ውድድር ክስተት በመሆን አቅም ካላቸው ቡድኖች በላይ የተሻለ ቡድን መሆኑን አስመልክቶናል። ሀሰተኛ አጥቂ በመሆን የውድድሩ ሦስተኛ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ ያጠናቀቀው ተስፈኛው አጥቂ ሄኖክ ኤርሚያስ በሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ጎል አስቆጥሮ ቡድኑን አነቃቅቷል። ሄኖክ በውድድር ዓመቱ ያስቆጠረውን ጎል መጠን 21 አድርሷል። ጎል በማስቆጠራቸው የተነሳሱት ዲኤፍቲዎች አቻ የሚያደርጋቸውን ሁለተኛ ጎላቸውን ኤሲ ሁሴን ከሳጥን ውጭ ጎል ማግኘት ችለዋል።

ተመጣጣኝ ፉክክር እየታየበት በቀጠለው በዚህ ጨዋታ የኤልፓው ተስፈኛ አጥቂ አብዱልከሪም ማሙሽ ከመስመር እየገፋ ተጫዋች ቀንሶ ወደ ሳጥን በመግበት በጥሩ አጨራረስ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሯል።

ጨዋታው በዚህ ውጤት ተጠናቀቀ ሲባል ተቀይሮ እየገባ ልዩነት በመፍጠር እና ጎል በማስቆጠር የሚታወቀው እዮሳፍጥ ግርማ ቡድኑን ከመሸነፍ የታደገች ሦስተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮ ኤሌትሪክ ሦስተኛ ደረጃ ይዞ ሲያጠናቅቅ ዲኤፍቲ ተከታዩን ደረጃ በመያዝ ውድድሩን አጠናቋል።

የዕለቱ ተጠባቂ ጨዋታ የሆነው የኢትዮጵያ መድን እና አዳማ ከተማ ጨዋታ አዳማ ከተማ በፍፁም የበላይነት አምስት ለዜሮ አሸናፊነት ተጠናቋል። የዕለቱ የክብር እንግዶች ተጫዋቾችን በመተዋወቅ በጀመረው በዚህ ጨዋታ ባሳለፍነው ረቡዕ ኢትዮጵያ መድን ከመከላከያ ጋር በነበረው ጨዋታ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች ሳላዲን አብደላ እና ዳዊት አውላቸው በቀይ ካርድ ምክንያት ቀጣይ ጨዋታ የሚያልፋቸው መሆኑ በቡድኑ ቀጣይ ውጤት ላይ ተፅዕኖ የሚያደርግ መሆኑ እንደገልፅነው ሁሉ የዛሬው ጨዋታ የመድን ሽንፈት ምክንያቱ የሁለቱ ተጫዋቾች አለመኖር መሆኑን ታዝበናል።

በአንፃሩ አዳማ ከተማ ከዚህ ቀደም በመጡበት ጥንካሬ ዛሬም ይዘው በመቅረብ ጨዋታውን ተቆጣጥረው ጎሎችን ማስቆጠር የጀመሩት ገና በጨዋታው ጅማሬ ዮሴፍ ታረቀኝ ራሱ በመጠቀም የሚችለውን ዕድል ለኃይለመልአክ አሰፋ አመቻችቶ በማቀበል ኃይለመላዕክ የጨዋታውን የመጀመርያ ጎል አስቆጥሯል። ጎል ቢቆጠርባቸውም መድኖች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ቢኖራቸውም ብቻውን ጥሩ ሲንቀሳቀስ በዋለው ባለ ግራ እግሩ ይትባረክ ሰጠኝ ሁለት የጎል ዕድሎችን በግሉ ቢፈጥርም ሳይሳካለት ቀርቷል።

በጥንቃቄ ሲጫወቱ የዋሉት አዳማዎች ከአንድ አጥቂ የሚጠበቀውን ነገር አሟልቶ በያዘው ዮሴፍ ታረቀኝ አማካኝነት ሁለተኛ ጎላቸውን በማስቆጠር ጨዋታውን መቆጣጠር ችለዋል። ከዕረፍት መልስ የአዳማን አጨዋወት መቆጣጠር የተሳናቸው መድኖች እጃቸውን ለአዳማ በመስጠት ተጨማሪ ጎሎችን ሊስተናገድባቸው ችሏል። የአዳማ ሁለተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ለቡድኑ ውጤት ማማር ትልቁን ሚና የተወጣው ሰይፈዲን ረሺድ በግል ጥረቱ በተከታታይ ሁለት ጎሎችን አስቆጥሮ የአዳማን የጎል መጠን ወደ አራት ከፍ አድርጓል።

በአዳማ አካባቢ በርከት ያሉ ታዳጊዎችን በማብቃት በሚታወቀው የአደማው ዋና አሰልጣኝ አፈወርቅ ከበደ ለሌሎች ተጫዋቾችን ዕድል በመስጠት ቀይሮ በማስገባት ቀሪውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሲቀጥሉ ልማደኛው አጥቂ ዮሴፍ ታረቀኝ ከጠባብ ቦታ መሬት ለመሬት በመምታት ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ አምስተኛ ጎል አስቆጥሯል። ዮሴፍ በውድድር ዓመቱ 28 ጎል በማስቆጠር ከሳላዲን አብደላ በሁለት ጎል አንሶ ሁለተኛ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን አጠናቋል። ከዚህ በኃላ በጨዋታው የተለየ ነገር ሳንመለከት በአደማ የበላይነት ጨዋታው አምስት ለዜሮ መጠናቀቅ ችሏል። ውጤቱን ተከትሎ አዳማ ከተማ በአስራ ሦስት ነጥብ የማጠቃለያው ውድድር አሸናፊ ሲሆን ኢትዮጵያ መድን ሁለተኛ ሆኗል።

አዳማ ከተማ በሁለቱም እድሜ እርከን ማለትም ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ እንዲሁም ከ17 ዓመት በታች ታዳጊ ቡድኑ በአንድ የውድድር ዓመት ቻምፒዮን መሆን የቻለ ሲሆን በቀጣይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚዘጋጀውን ከ17 ዓመት በታች ውድድር ማሸነፍ ከቻለ ከዚህ ቀደም በ2009 ሀዋሳ ከተማ ያሳካውን ድል የሚጋራ ይሆናል።

በማስከተል ለመርሐግብር ማሟያ ኢትዮጵያ ቡና እና መከላከያ ያደረጉት ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና ሁለት ለዜሮ አሸናፊነት ተጠናቋል። ለቡናማዎቹ ዮሐንስ መንግስቱ እና አቤል ፀጋዬ ናቸው ጎሎቹን ያስቆጠሩት።

* የውድድር ቻምፒዮን ለሆነው ቡድን የሜዳልያ እና ዋንጫ እንዲሁም ለኮከብ ተጫዋች እና ጎል አግቢ የሽልማት አሰጣጥ መርሐግብር የፊታችን እሁድ ሰኔ 6 ቀን በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ከማለዳ ጀምሮ በሚካሄደው የመዝጊያ ሥነ ስርዓት የሚበረከት ይሆናል።