ከፍተኛ ሊጉ መውረዱን ያረጋገጠ ቢሆንም በቅርቡ እንደ አማራጭ በቀረበው የዙር ውድድር ላይ ለመሳተፍ ዕድል ያገኘው ወልቂጤ ከተማ የዓመቱ አራተኛ አሰልጣኝ ወደ ክለቡ አምጥቷል፡፡
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ አጀማመሩ ያማረ ቢመስልም በመጨረሻ ግን ከሊጉ መውረዱን ያረጋገጠው ወልቂጤ በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው እየተመራ ዓመቱን ቢጀምርም አሰልጣኙ ባጋጠማቸው ህመም ምክንያት ከክለቡ ጋር የተለያዩ ይመሰላል፡፡ ክለቡም የቀሩትን ጨዋታዎች በምክትል አሰልጣኝ አብዱልሀኒ ተሰማ ከዘለቀ በኃላ አሁንም ግልፅ ባልሆነ ምክንያት በአብዱልሀኒ ምትክ አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሃን ቡድኑ እስከወረደበት ጊዜ ድረስ ሲመራ መቆየቱ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የትግራይ ክልል ክለቦች በ2014 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የማይሳተፉ ከሆነ ባዘጋጀው ሁለተኛ አማራጭ መነሻነት ቡድኑ ሰኔ 18 በሀዋሳ ለሚጀመረው ውድድር ላይ ተሳትፎን በማድረግ ዕድሉን ለመሞከር በዓመቱ በአራተኛ አሰልጣኝ ሊመራ ዝግጅቱን ጀምሯል፡፡ አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ወልቂጤን በዚህ ውድድር ላይ ለመምራት ኃላፊነት መውሰዳቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና፣ ሀዲያ ሆሳዕና፣ ባህር ዳር ከተማ አሰልጣኝ እና ከሰበተኛው ሳምንት ጨዋታ በኋላ ከጅማ አባጅፋር ጋር የተለያዩት አሰልጣኝ ጳውሎስ ምን ይህል ቆይታ በሠራተኞቹ ቤት ይኖራቸዋል የሚለው ጉዳይ ግልፅ ባይሆኑም ቡድኑን መረከባቸውን ሰምተናል፡፡
ይህን ዘገባ ባጠናከርንበት ወቅት አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ከአዲስ አበባ ሆሊደይ ሆቴል በመነሳት ቡድኑን እየመሩ ውድድሩ ወደሚስተናገድባት ከተማ ሀዋሳ ጉዞ መጀመራቸውን አረጋግጠናል።