ከትናንት በስቲያ ለሴካፋ ዋንጫ ቅድመ ዝግጅቱን የጀመረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ክለባቸው በሄዱ ተጫዋቾች ምትክ ሌሎችን ተክቷል።
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በባህርዳር ለሚደረገው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ (ሴካፋ) ውድድር ለ35 ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ ቡድኑ ለቅድመ ውድድር ዝግጅት ከትላንት በስቲያ ጀምሮ በካፍ የልህቀት ማዕከል በመሰብሰብ ልምምድ የጀመረ ሲሆን ከቀናት በኋላም ወደ ንግድ ባንክ ሜዳ ያመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ በዝግጅቱ ከተጠሩ ተጫዋቾች ውስጥ በሁለት ምክንያቶች ስምንት ተጫዋቾች ከብሔራዊ ቡድኑ ውጪ መሆናቸውን ከቀናት በፊት መግለፃችን ይታወሳል፡፡ ይህንንም ተከትሎ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ተጨማሪ ተጫዋቾች ስለሚያስፈልጉ በሚል በተጠባባቂነት ተይዘው የነበሩ ሁለት ተጫዋቾችን ወደ ዝግጅታቸው ቀላቅለዋል።
በሀዋሳ ከተማ ከታችኛው ቡድን አድጎ ያለፉትን አምስት ዓመታት ሲጫወት የቆየው እና ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ ተጫውቶ ያሳለፈው ሁለገቡ የመስመር ተጫዋች ዮሐንስ ሱጌቦ አንደኛው ተጫዋች ነው። ሁለተኛው ደግሞ በአሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ በሚመራው ኢትዮጵያ መድን ዘንድሮ ከ17 ዓመት በታች ቡድን አድጎ በከፍተኛ ሊጉ ድንቅ የውድድር ዓመትን አሳልፎ የነበረው አጥቂው መሐመድኑር ናስር ሆኗል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የብሔራዊ ቡድኑ የስብስብ ብዛት ወደ 29 ከፍ ብሏል፡፡