በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የሴካፋ ዋንጫ እየተዘጋጀ የሚገኘው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የአቋም መለኪያ ጨዋታ አድርጓል።
በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ቡድን ከሳምንት በፊት 28 ተጫዋቾችን በመያዝ አያት በሚገኘው የካፍ የልህቀት ማዕከል ሲዘጋጅ መቆየቱ ይታወቃል። በዛሬው ዕለትም የመጨረሻዎቹን ተጫዋቾችን ለመለየት በአዲስ አበባ ስታዲየም ረፋድ ላይ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ አድርጓል።
ለሁለት ተከፍሎ ለሁለት ሰዓት በተካሄደው በዚህ ጨዋታ በመጀመርያው ቡድን ውስጥ ታምራት ዳኜ፣ አማኑኤል ተርፉ፣ ኃይለሚካኤል አደፍርስ፣ ፀጋሰው ድማሙ፣ አማኑኤል እንዳለ፣ ኤርሚያስ በላይ፣ በረከት ወልዴ፣ ወንድማገኝ ኃይሉ፣ ዱሬሳ ሹቢሳ፣ መሐመድኑር ናስር እና ስንታየሁ መንግስቱ መጫወት ችለዋል። በዚህ አጋማሽ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተስፈኛ ተከላካይ አማኑኤል ተርፋ ጉዳት አስተናግዶ ጨዋታውን አቋርጦ የወጣ ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በፍፁም ቅጣት ምት ጎል አንድ ለዜሮ እየመሩ ወደ እረፍት አምርተዋል።
አሰልጣኝ ውበቱ በሁለተኛው ቡድን ፋሲል ገብረ ሚካኤል፣ ሰለሞን ወዴሳ፣ መናፍ ዐወል፣ ኃይሌ ገብረትንሳኤ፣ ዮሐንስ ሴጌቦ፣ ኪሩቤል ኃይሉ፣ ዊሊያም ሰለሞን፣ አብዱልአዚዝ ቶፊቅ፣ ሙኅዲን ሙሳ፣ መስፍን ታፋሰ እና ብሩክ በየነ ተጠቅመዋል። በዚህ አጋማሽ ደግሞ መስፍን ታፈሰ ለብሔራዊ ቡድኑ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
የቀሩትን ተጫዋቾች አሰልጣኝ ውበቱ ቀይረው በማስገባት ሲጠቀሙ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ፣ ዓለምብርሀን ይግዛው እና ቸርነት ጉግሳ ጉዳት በሚመሰል ሁኔታ የጨዋታው አካል ሳይሆኑ ተነጥለው ብቻቸውን ቀለል ያለ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ታይተዋል።
በቅርቡ ወደ ባህር ዳር የሚያቀናው ብሔራዊ ቡድኑ የመጨረሻ ተመራጭ እጩዎችን በቀጣይ የሚሳውቅ ይሆናል።