የአሠልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባጅፋር 0-0 ወልቂጤ ከተማ

ረፋድ ላይ የተደረገው ጨዋታ ያለ ግብ ከተጠናቀቀ በኋላ ሶከር ኢትዮጵያ ከአሠልጣኞች የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ተቀብላለች።

ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ጅማ አባጅፋር

ስለ ጨዋታው?

ጨዋታው ውጥረት ነበረው። ቀላል ጨዋታ አልነበረም። ወልቂጤ በኳስ ቁጥጥር፣ በፍጥነት፣ በአካል ብቃትም ሆነ አብሮ በመቆየት የተዋሀደ ቡድን ነው። እኛም በጣም ጥንቃቄ አድርገን ለመጫወት ሞክረናል። የእኛ ቡድን ከአንድ ወር በኋላ ነው ወደ ጨዋታ የተመለሰው። ይሄ ቢሆንም የዛሬው ግጥሚያ ለጨዋታ ዝግጁነታችን (Match fitness) ጠቅሞናል። በአጠቃላይ ከባዱን ፈተና ተወተናል ብዬ እገምታለሁ።

የግብ አጋጣሚዎችን ስላለመጠቀማቸው?

የመከላከል አደረጃጀታችም ዛሬ ጥሩ ነበር። ወደ ጎልም እየደረስን ነው ያለነው። ግን የወልቂጤ ተከላካዮችም ጠጣር የመሆን ባህሪ ነበራቸው። እኛ በተቻለ መጠን ጎል ላይ ለመድረስ ሞክረናል። አጨራረሳችንን ማሳመር ደግሞ የውዴታ ግዴታችን ነው። አንድ ነጥብ ለእኛ ብዙም አስፈላጊያችን አይደለም። ስለዚህ ጎል ማግባት አለብን። ዛሬ ግን ትልቅ ጨዋታ ነበር የገጠመን። ተጋጣሚያችን ክብር ከምንሰጠው ቡድን ነው። በቀጣይ ጨዋታዎች ላይ ደግሞ አጨራረሳችንን እናስተካክላለን።

ጳውሎስ ጌታቸው – ወልቂጤ ከተማ

ስለ ጨዋታው?

ጨዋታው በጣም ጥሩ ጨዋታ ነበር። ኳሱን በጣም ተቆጣጥረን 90 ደቂቃ ለመጫወት ሞክረናል። ያገኘነውን አጋጣሚ አለመጠቀማችን ግን ዋጋ አስከፍሎናል። ግን እንደተመለከታችሁት ቡድኑ ቶሎ ቶሎ ጎል ጋር ይደርሳል። በሚቀጥለው ጨዋታ ግን የዛሬውን ችግር አርመን በደንብ ተዘጋጅተን በፕሪምየር ሊጉ ላይ ለመቆየት እንሞክራለን።

ያገኟቸው የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ስላለመጠቀማቸው?

በራስ የመተማመን እጥረት ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ተጫዋቾቹ ከሽንፈቶች ስለመጡ የነበረውን ነገር ለማረም ጉጉት ነበራቸው። ጨዋታውም ላይ አጋጣሚዎችን ያልተጠቀምነው ከጉጉት የተነሳ ነው። በአጠቃላይ ዋናው ቁምነገሩ የቡድኑ የአጨዋወት ዘይቤ ምን ይመስላል የሚለውን ማሳየት ነው። ይሄንን ችግር በሚቀጥለው ጨዋታ ቀርፈን እንመጣለን።