በሻላ የጤና ቡድን አዘጋጅነት ታላቁ አጥቂ አሰግድ ተስፋዬን ለመዘከር የተሰናዳው ውድድር ላይ አበበ ቢቂላ እና ኢትዮ አፍሪካ ለፍፃሜ ጨዋታ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።
እጅግ ቁጥር በርከት ያለ ተመልካች በታደመበት የዛሬው የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ አስቀድሞ በስምንት ሰዓት አበበ ቢቂላ እግርኳስ ማኅበር ከሻላ እግርኳስ ማኅበር አገናኝቶ ጨዋታው ተዝናኖትን ፈጥሮ በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አንድ አቻ በመጠናቀቁ በመለያ ምት አበበ ቢቂላ ወደ ፍፃሜው ጨዋታ አላፊ ሆኗል።
የቀድሞ ምርጥ ተጫዋቾች በሁለቱም ቡድኖች በኩል የተገኙበትን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ የመሩት ሲሆን ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት ሻላዎች ነበሩ። ከማዕዘን ምት የተሻገረው ኳስ በተከላካዮች ተደርቦ ሲመለስ በቅርበት የነበረው የቀድሞ የመከላከያ እና ደደቢት ድንቅ ተከላካይ መንግሥቱ አሰፋ (ማሲንቆ) አስቆጥሮ ሻላዎች መምራት ጀምረዋል። ይህም ቢሆን ሻላዎች ደስታቸውን አጣጥመው ሳይጨርሱ ወድያውኑ ለአበበ ቢቂላ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ወሳኝ ገብሬ አስቆጥሮ አቻ መሆን ችለዋል። ሁለቱም ቡድኖች ጥንቃቄ መርጠው ውጥረት በተሞላበት ጨዋታ ቀጥለው በተለይ ሻላዎች በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ግልፅ የጎል አጋጣሚ በምንያህል ተሾመ አማካኝነት ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት የቀረው ዕድል የሚያስቆጭ ሆኖ ነበር።
ጨዋታውም በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አንድ አቻ ተጠናቆ ወደ መለያ ምት አምርቶ የሚያመክን ተጫዋች ጠፍቶ በመጨረሻም የሻላው ግብጠባቂ በመሳቱ ምክንያት ጨዋታው 9-8 በሆነ ውጤት በአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚመራው አበበ ቢቂላ ወደ ፍፃሜ ጨዋታው አላፊ መሆን ችሏል።
በማስከተል አስር ሰዓት ላይ ኢትዮ አፍሪካን ከ11 ቀበሌ ሜዳ ያደረጉት ጨዋታ መደበኛው ጨዋታ ክፍለ ጊዜ አንድ አቻ በመጠናቀቁ ወደ መለያ ምት አምርቶ ኢትዮ አፍሪካኖች 5-4 በሆነ ውጤት በማሸፍ ወደ ፍፃሜ ጨዋታ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።
ጥሩ የኳስ ፍሰት በታየበት የአመሻሹ ጨዋታ የሁለቱም ቡድኖች ግብጠባቂዎች ብቃት የተፈጠሩ የጎል ዕድሎችን በማምከናቸው በመጀመርያው አጋማሽ ጎል ሳንመለከት ቀርተናል። ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተጋግሎ ቀጥሎ በበርካታ ደጋፊዎቻቸው ታጅበው የሚጫወቱት 11 ቀበሌ ሜዳዎች በዮሴፍ አምሐ አማካኝነት ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ባስቆጠሩት ጎል የተነቃቁት አስራ አንድ ሜዳዎች ተጨማሪ እድሎችን አግኝተው የነበረ ቢሆንም ከዚህ ቀደም በተለያዩ ክለቦች እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምናውቀው የአሁኑ የቅዱስ ጊዮርጊስ የግብጠባቂ አሰልጣኝ ውብሸት ደሳለኝ አድኖባቸዋል።
ኢትዮ አፍሪካዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያደረጉት ከፍተኛ ጥረት ተሳክቶ ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ በልሁ ኃይሉ በእግሩ ደገፍ አድርጎ ጎል አስቆጥሮ አቻ አድርጓቸዋል። ጨዋታው ወደ መለያ ምት አምርቶ የኢትዮ አፍሪካው ግብጠባቂው ውብሸት ደሳለኝ ባዳናት ኳስ 5–4 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ኢትዮ አፍሪካዎች ቅዳሜ ለሚካሄደው የፍፃሜ ጨዋታ አላፊ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በዛሬው ጨዋታ ባልተጠበቀ ሁኔታ ሁለት የውጭ ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች በአሰግድ የመታሰቢያ ውድድር በሻላ ቡድን እና በ11 ሜዳ ቡድኖች ተመልክተናል።
የፊታችን ቅዳሜ ሰኔ 12 ቀን ከጠዋቱ 03:00 በሚካሄደው የኢትዮ አፍሪካ እና የአበበ ቢቂላ የፍፃሜ ጨዋታ የአሰግድ ተስፋዬ ቤተሰቦች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የሚታደሙበት ይሆናል። ከፍፃሜው ጨዋታ ባሻገር ለውድድሩ ኮከቦች ሽልማት እንደሚበረከትም ሰምተናል።