የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አምስት አዲስ ተጫዋቾቹን ጨምሮ ዝግጅቱን ማድረጉን ቀጥሏል።
ብሔራዊ ቡድኑ በቅርቡ የሰባት ተጫዋቾ በመቀነስ እንዲሁም አዲስ አምስት ተጫዋቾችን በማካተት በአጠቃላይ 25 ተጫዋቾችን ይዞ ረፋድ ላይ በንግድ ባንክ ሜዳ ለሁለት ሰዓት ያህል ልምምዱን ሰርቷል።
ትናንት ብሔራዊ ቡድኑ የተቀላቀሉት ምንተስኖት አሎ፣ ፅዮን መርዕድ፣ ዳዊት ተፈራ፣ ሀብታሙ ተከስተ እና አቡበከር ናስር በስብስቡ ውስጥ መካተታቸው አስቀድሞ በየቦታው ይታይ የነበረው ክፍተት ላይ ጥራት መጨመራቸውን ታዝበናል።
ከቀናት በፊት ከተቀነሱት ሰባት ተጫዋቾች መካከል ስሙ ያልተጠቀሰው የፋሲል ከነማው አማካይ ኩርቤል ኃይሉ በዛሬው ልምምድ ወቅት ከቡድኑ አባላት ጋር አልተመለከትነውም። ኪሩቤል ከኢትዮ ኤሌትሪክ ጋር በነበረው ጨዋታ መጠነኛ ጉዳት አጋጥሞት የቡድኑ ማረፊያ የካፍ የልሕቀት ማዕከል እንደሚገኝ ሰምተናል።
ሙሉ ዘጠና ደቂቃ ለሁለት ተከፍሎ ጨዋታ በተከናወነበት የዛሬው ልምምድ አቡበከር ናስር እና ሀብታሙ ተከስተ የጨዋታው አካል ሳይሆኑ ለብቻቸው ተነጥለው ሙሉ ሜዳውን ለተወሰነ ደቂቃ ሲሮጡ ተመልክተናል።
የብሔራዊ ቡድኑ ስብስብ ከቀን ወደ ቀን እየተቀናጀ እንደመጣ ባስመለከተን በዛሬው ጨዋታ ወቅት ዊልያም ሰለሞን ከጉዳቱ ጋር እየታገለ ጨዋታውን ጨርሶ ሲወጣ ታዝበናል። የልምምዱ ሙሉ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ እንደተጠናቀቀ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ፣ ዮሐንስ ሰጌቦ፣ ሙኽዲን ሙሳ፣ ብሩክ በየነ፣ መናፍ ዐወል፣ ቸርነት ጉግሳ እና ኃይሌ ገብረትንሳይን ነጥለው የሰውነት ክብደታቸውን እንዲያስተካክሉ ለብቻቸው ፈጣን ሩጫ ሲያስሮጧቸው አይተናል።
ሐሙስ ወደ ባህር ዳር እንደሚያቀና የሚጠበቀው ቡድኑ በአጠቃላይ ዝግጅታቸውን አስመልክቶ ከደቂቃዎች በኃላ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ ይታወቃል።