“በሀገራችን በሚዘጋጀው ውድድር ላይ ….” – ወበቱ አባተ

በሴካፋ ውድድር የሚሳተፈውን የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንን በተመለከተ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ መግለጫ ሰጥተዋል።

ከሰኔ 26 እስከ ሐምሌ 12 ድረስ በባህር ዳር ከተማ የሚደረገው የምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ዋንጫ (ሴካፋ) ውድድር ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሰኔ 4 ጀምሮ መቀመጫውን በካፍ የልህቀት ማዕከል በማድረግ ዝግጅቱን እየሰራ ይገኛል። ባለበት የካፍ ማዕከል እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ ልምምዱን ሲሰራ የቆየው ስብስቡም ባሳለፍነው ቅዳሜ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል። ይሄንን የዝግጅት ጊዜ እና ቅዳሜ ረፋድ የተደረገውን የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ጨምሮ ቡድኑ ላይ ያሉትን ጉዳዮች በተመለከተም የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ለብዙሃን መገናኛ አባላት መግለጫ ሰጥተዋል። አሠልጣኙም ከዋናው ብሔራዊ ቡድን ጎን ለጎን ከ23 ዓመት በታች ቡድኑን ለማሰልጠን የቻሉበትን ሁኔታ በማስረዳት ንግግራቸውን ጀምረዋል።

“እኛ የኢትዮጵያ ዋናው ብሔራዊ ቡድንን ለማሰልጠን ነው ወደ ቦታው የመጣነው። ግን ከታችኛው ብሔራዊ ቡድን (ከ17 ዓመት በታች) ጀምሮ እስከ ኦሎምፒክ ቡድኑ (ከ23 ዓመት በታች) ድረስ ያሉ የእድሜ እርከን ቡድኖች በተመሳሳይ የጨዋታ መንገድ እንዲጫወቱ የማድረግ ስራ ተጀምሯል። በሴካፋ ውድድር የሚሳተፈው ከ23 ዓመት በታች ቡድን ደግሞ ለዋናው ብሔራዊ ቡድን ቅርብ እንደሆነ ይታወቃል። ከዚህም መነሻነት በዋናነት በቀጣዮቹ ስድስት እና ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያን የሚያገለግሉ ተጫዋቾችን ለማዘጋጀት እና ቀጣይነት ያለው ቡድን ለመገንባት ነው ስራው እየተሰራ ያለው።” በማለት ከዋናው ብሔራዊ ቡድን ወረድ ብለው ከ23 ዓመት በታች ቡድኑን በመያዝ እየሰሩት ያለውን ስራ ገልፀዋል። አያይዘውም ቡድኑ በሌላ አሠልጣኝ ቢያዝ ጥሩ መሆኑን አውስተው ‘ዋናው ብሔራዊ ቡድን ላይ የታየውን ተስፋ ወደ ታች ብናወርድ ሀገር ትጠቀማለች’ በሚል ሀሳብ ቦታውን እንደያዙም አስረድተዋል።

አሠልጣኙ ቀጥለውም ተጫዋቾች የመረጡበትን ሂደት ማብራራት ይዘዋል።

“ምርጫውን በተመለከተ በፕሪምየር ሊጉ ላይ ያሉ ወጣት ተጫዋቾችን ከየቡድኖቹ ለመመልከት ሞክረናል። በመጀመሪያም 35 ተጫዋቾችን ጠርተናል። ከ35ቱ ደግሞ 5 ተጫዋቾች ከታችኛው ሊግ የተመረጡ ናቸው። ከሰኔ 4 ጀምሮም ልምምዳችንን በካፍ የልህቀት ማዕከል ስንሰራ ነበር። ተጫዋቾቹ እንደተሰበሰቡም የቅድመ ምርመራ እና የአካል ብቃት ፍተሻ ከተደረገ በኋላ በቶሎ መደበኛ ዝግጅታችንን ጀምረናል። ግን ከጠራናቸው 35 ተጫዋቾች ማግኘት የቻልነው 29ኙን ነው። ምክንያቱም ቀሪዎቹ እንደ አጋጣሚ ከ23 ዓመት በላይ ስለሆኑ።

“አንድ ሳምንት ከሰራን በኋላ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ክለብ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አድርገናል። ጨዋታውን በሰኔ 12 ካደረግብ በኋላ በህመም፣ በጉዳት እና በአቋም ስምንት ተጫዋቾችን ቀንሰናል። ስምንቱን ቀንሰን ደግሞ አምስት አዳዲስ ተጫዋቾችን አካተናል። የተቀነሱት ተጫዋቾች
ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ (በህመም)፣ ዓለምብርሀን ይግዛው (ባልተገለፀ ጉዳት) ፣ ደስታ ዋሚሾ (በአቋም)፣ ኤርሚያስ በላይ (በአቋም) ፣ መሐመድኑር ናስር (በአቋም) እና ታምራት ዳኜ (በጡንቻ ጉዳት) አማኑኤል ተረፍ (ጉዳት) እንዲሁም ኪሩቤል ኃይሉ (በጉልበት ጉዳት) ናቸው። እንደ አዲስ የተካተቱት ደግሞ ምንተስኖት አሎ፣ ፅዮን መርዕድ፣ አቡበከር ናስር፣ ሀብታሙ ተከስተ እና ዳዊት ተፈራ ናቸው። አሁን ላይ 25 ተጫዋቾች አሉን። የመጨረሻ ምዕራፍ ዝግጅታችንን እነዚሁ 25 ተጫዋቾች ይዘን እንሰራለን። ከነገ በስትያ ደግሞ ውድድሩ ወደሚደረግበት ባህር ዳር እናቀናለን። በሴካፋ ህግ 23 ተጫዋቾችን ነው መያዝ የሚቻለው። ስለዚህ የኮቪድ እና የጉዳት ጉዳዮችን በማገናዘብ እስከ መጨረሻው ዕለት እነዚሁ ተጫዋቾች ይዘን ከቀጠልን በኋላ ስም ማስገባት በሚኖርብን ጊዜ ሁለት ተጫዋቾችን ቀንሰን የመጨረሻ 23 ተጫዋቾችን እንለያለን።” ብለዋል።

አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከሰኔ 26 – ሐምሌ 12 ድረስ በባህር ዳር በሚካሄደው ውድድር ላይ የቡድኑን የአጭር ጊዜ ግብ በአጭሩ እንዲህ ብለው አስቀምጠዋል። “በሀገራችን በሚዘጋጀው ውድድር ላይ የተሻለ ፉክክር ለማድረግ እና ጥሩ ውጤት ለማምጣት እንሰራለን።”

ውበቱ አባተ ገለፃቸውን ከጨረሱ በኋላም በስፍራው ከተገኙት ከ10 ከማይበልጡ የብዙሃን መገናኛ አባላት ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ምላሽ መስጠት ጀምረዋል።

ምርጫው በፕሪምየር ሊጉ ላይ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን በአብዛኛው ስለማካተቱ?

“ልክ ነው። የተጫዋች ምርጫው በአብዛኛው በፕሪምየር ሊጉ ላይ ወደሚጫወቱ ተጫዋቾች ያደላ ነው። ግን እኛ ዋናውን ብሔራዊ ቡድን ለማዘጋጀት ትኩረት ሰጥተን ስንመለከተው የነበረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ነው። ይህ ቢሆንም ግን በከፍተኛ ሊጉ ጥሩ ብቃት አሳይተዋል የተባሉ ተጫዋቾችንም ለማካተት ተሞክሯል። በተለይ በከፍተኛ ሊጉ የሚያሰለጥኑ አሠልጣኞችን በማናገር ጥሩ ብቃት ያሳዩትን ለመምረጥ እና ለማየት ችለናል። ግን ጊዜ ኖሮን እስከ ታችኛው የሊግ እርከን ብንሄድ ጥሩ ነበር።”

በሴካፋው ውድድር ቡድኑ እስከ የት ድረስ መጓዝ ይችላል?

“የሌሎች ቡድኖችን አቋም ሳናይ መናገር ትንሽ የሚከብድ ይመስለኛል። በውድድሩ ታሪክ ብዙ ዋንጫ ያገኙ ሀገራትን ማወቅ ሊቻል ይችላል። ግን የዘንድሮ ውድድር በአዲስ ሁኔታ ከ23 ዓመት በታች ተጫዋቾች የሚሳተፉበት ነው። ስለዚህ ለየት ያለ ነው። በውድድሩ ላይ የሚሳተፉት አስራ አንድ ሀገራት ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታም በደንብ ሳያውቁ እቅድ ማስቀመጥ አግባብ ያለው አይመስለኝም።”

በልምምድ እና በአቋም መለኪያ ጨዋታው ቡድኑ ላይ ስላዩት ነገር?

“በተወሰነ መልኩ የአካል ብቃት ዝግጁነት ችግር አንዳንድ ተጫዋቾች ላይ አይቻለሁ። ከዚህ ውጪ ግን እንድንጫወትበት የምንፈልገውን የጨዋታ መንገድ በሜዳም ሆነ በክፍል ውስጥ እያሳየናቸው ነው። የተለየ ቡድኑ ላይ ያየሁት ነገር ግን ጉጉት ነው። ተጫዋቾቹ የሆነ ነገር አድርጎ ለማሳየት የርሃብ አይነት ነገር አይባቸዋለሁ። በአጠቃላይ ቡድኑ ላይ እያየሁት ባለው ነገር ደስተኛ ነኝ። በቀጣይ ዓመታት በደንብ ኢትዮጵያን ሊያገለግሉ እንደሚችሉም ተረድቻለሁ። እንደ ክፍተት ግን የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ብናገኝ ጥሩ ይሆን ነበር። ግን ተጫዋቾቹ ላይ ያለው ነገር ከበቂ በላይ ነው።”

ቡድኑ ስለሚጫወትበት የጨዋታ መንገድ?

“እኛ ተጫዋቾቹን በአምሮም ሆነ በአካል ብቁ እንዲሆኑ እያዘጋጀናቸው ነው። ለቀጣዮቹ ዓመታት እንዲጠቅሙ ነው እያዘጋጀናቸው ያለነው። ግን በጨዋታ መንገድ ዙሪያ ለእኛ የሚያዋጣንን መምረጡ ወሳኝ ይመስለኛል። በጨዋታ ወቅት እንደሚኖር ነገር መቀያየሩ ሊኖር ይችላል። ግን ወሳኙ ነገር ዋናውን ብሔራዊ ቡድን የሚመስል ቡድን ለማምጣት እየተሰራ ነው። ዋናው ቡድን በሚጫወትበት መንገድ ነው ይሄኛውም ቡድን እንዲጫወት የምንፈልገው።”