በቀጣይ ዓመት የትግራይ ክልል ክለቦች በሊጉ የማይሳተፉ ከሆነ እነሱን ለመተካት የሚደረገው የስድስት ክለቦች ውድድር ከዓርብ ጀምሮ ይከናወናል።
በዘንድሮ የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ያልተሳተፉት መቐለ 70 እንደርታ፣ ስሑል ሽረ እና ወልዋሎ ዓ/ዩ በቀጣይ ዓመት በሚኖረው ውድድር ላይ መመለሳቸው እሳካሁል አልታወቀም። የሦስቱ ክለቦች ጉዳይ እየተጠበቀ ጎን ለጎን ክለቦቹ በሊጉ ለመሳተፍ ፍቃድ ካልሰጡ ግን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ዘንድሮ ከሊጉ የወረዱት ሦስት ክለቦች (ወልቂጤ ከተማ፣ ጅማ አባጅፋር እና አዳማ ከተማ) እና ከከፍተኛ ሊግ ሦስት ምድቦች ሁለተኛ የወጡት ክለቦች (ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከ፣ ሀምበሪቾ ዱራሜ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ) ከአርብ ሰኔ 18 ጀምሮ የአንድ ዙር የነጥብ ጨዋታ በማድረግ ቦታውን ለመያዝ ፍልሚያ ያከናውናሉ።
ይሄንን የስድስት ክለቦች ውድድር በበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንም ልዩ ትኩረት በመስጠት የቅድመ – ውድድር ሥራዎችን እየከወነ እንደሆነ ተጠቁሟል። በተለይም በውድድሩ ከዳኝነት ጋር የሚያያዙ እንከኖች እንዳይኖሩት ልምድ እንዲሁም ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን የመዳኘት ብቃት ያላቸው ዋና እና ረዳት ዳኞች መመረጣቸው ተነግሯል። ከዚህ ውጪ ሀዋሳ ላይ የሚስተካከሉ ጥቃቅን ነገሮችን ለማስተካከል ደግሞ ለውድድሩ የተዋቀረው ኮሚቴ በዛሬው ዕለት ወደ ስፍራው (ሀዋሳ) እንደሚጓዝ ሰምተናል።
ከሰኔ 18 እስከ ሐምሌ 4 ድረስ እንደሚደረግ መርሐ-ግብር የወጣለት ውድድሩም በቀን ሦስት ጨዋታዎች እንደሚከወኑበት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። የውድድሩ የእጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓትም በውድድሩ ቀን ዋዜማ (ሀሙስ ከሰዓት) እዛው ሀዋሳ ተሳታፊ ክለቦቹ ባሉበት የሚወጣ ይሆናል።