በኢትዮጵያ እና እስራኤል እግርኳስ ፌዴሬሽኖች መካከል በተፈጠረው እግርኳሳዎ ግንኙነት ሁለቱ አካላት አብሮ ለመስራት ይፋዊ ስምምነት ፈፅመዋል።
በአቶ ኢሳይያስ ጂራ የሚመራው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ለክለቦች አሳልፎ ከሰጠ በኋላ ትኩረቱን ለብሔራዊ ቡድኖች እና ልማታዊ ጉዳዮች ላይ በማድረግ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል። ከእግርኳስ ልማታዊ እንቅስዋሴዎች አንዱ የሆነውን ስምምነት ደግሞ ከደቂቃዎች በፊት በእስራኤል መፈፀሙ ከስፍራው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
ከወራቶች በፊት ከእስራኤል እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር ግንኙነት የጀመረው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ውጥኑ ፍሬ አፍርቶ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን እንዲያገኝ ሆኗል። ከአቋም መፈተሻ ጨዋታዎቹ በተጨማሪ ሁለቱ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች በእግርኳስ የልማት እንዲሁም የቴክኒካዊ ጉዳዮች አብረው ለመስራት የሚያስችላቸው ስምምነት ላይ ደርሰው ተፈራርመዋል። ከደቂቃዎች በፊትም በስፍራው የሚገኙት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ እና የጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን በኢትዮጵያ በኩል እንዲሁም የእስራኤል እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኦረን ሀሰን ደግሞ በእስራኤል በኩል ተገኝተው ስምምነቱን መፈፀማቸው ታውቋል። በፊርማ ሥነ-ስርዓቱ ላይም በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አቶ ዓለሙ ረታ ተገኝተው ነበር። የሁለቱ ሀገራት ስምምነት ዝርዝር ጉዳዮችም በቅርቡ በሚሰጥ ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚብራራ ተጠቁሟል።
በተያያዘ ዜና ማክሰኞ ምሽት የመጀመሪያ የአቋም መፈተሻ ጨዋታውን የከወነው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ቡድን ከዛሬው ሁለተኛ ጨዋታ በፊት በትናንትናው ዕለት ልምምዱን መስራቱ ተሰምቷል። አምስት ሰዓት ላይ ቡድኑ ልምምዱን ከሰራ በኋላም አመሻሽ ላይ በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ዓለሙ ረታ የእራት ግብዣ እንደተደረገለት ታውቋል። አምባሳደር ዓለሙ ረታ ቡድኑን ማበረታታቸው እና 5 ሰዓት በሚጀምረው ጨዋታ ላይም ሜዳ እንደሚገኙ እንደገለፁ አረጋግጠናል። ለሁለቱ ጨዋታዎች እና ለስምምነቱ እሁድ እኩለ ለሊት ወደ እስራኤል ያመራው ልዑካን ቡድንም ዛሬ ለሊት 7 ሰዓት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለስ ተነግሮናል።