ሪፖርት | ወልቂጤ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር ያለ ጎል አቻ ተለያይተዋል

የትግራይ ክልል ክለቦች በፕሪምየር ሊጉ ተሳታፊ ካልሆኑ እነሱን ለመተካት የሚደረገው ጨዋታ ዛሬ ሲጀመር ወልቂጤ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር ያለ ጎል 0ለ0 አቻ ተለያይተዋል፡፡

የመክፈቻው ጨዋታው ከመካሄዱ በፊት ክለቦቹ በተያዘላቸው ሰዓት ስታዲየም ቢደርሱም አስቀድሞ ሜዳው ለውድድር ብቁ ባለመሆኑ እና ወደ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ጊቢው በጥበቃ አካላት እንዲሁም የዩኒቨርስቲው የበላይ አመራሮች አትገቡም በማለታቸው ክለቦቹ በር ላይ ለመጠበቅ ሲገደዱ አይተናል። ሁለቱ ክለቦችም ከስታዲየሙ ቅጥር ግቢ ውጪ ከአንድ ሰዓት በላይ ለመቆም ተገደዋል፡፡ ላለመግባታቸው እንደ ምክንያት የቀረበው ደግሞ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ በሀዋሳ ሲደረግ ለስታዲየሙ ሠራተኞች ክፍያ ባለመፈፀሙ የተነሳ እንደሆነ የተገለፀልን ሲሆን በሲዳማ ክልል በተደረገ ርብርብ ግን የዚህ ውድድር አወዳዳሪ አካላት ከዩኒቨርስቲው ጋር ማንኛውንም ክፍያ ለመፈፀም በፊርማ እንዲስማሙ ከተደረገ በኋላ 3፡00 እንዲጀምር መርሐ-ግብር ወጥቶለት የነበረው ጨዋታ ከአንድ ሰዓት በላይ ዘግይቶ ሊጀመር ችሏል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የሥራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ እና አቶ አበበ ገላጋይ ከሌሎች የክብር እንግደዶች ጋር በጋራ በመሆን 4፡38 ሲል የወልቂጤ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር ተጫዋቾችን ከተዋወቁ በኋላ ጨዋታው ተጀምሯል፡፡ ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ የተስተዋለበት የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ወልቂጤ ከተማ በአንፃራዊነት ሻል ብሎ በመታየት ሙከራዎችን ሲያደርግ ታይቷል። በተለይ ፍሬው ሰለሞን እና አብዱልከሪም ወርቁ መሐል ሜዳ ላይ በሚፈጥሩት የአንድ ሁለት ቅብብል እና ወደ መስመር ባደላ እንቅስቃሴ ቡድኑ ወደ ጅማ አባ ጅፋር የግብ ክልል ለመጠጋት ጥረት ሲያደርግ ነበር፡፡ በዚህም በ9ኛው ደቂቃ ተስፋዬ ነጋሽ በቀኝ መስመር ከአብዱልከሪም ወርቁ ጋር በፈጠረው መናበብ ለአሜ የደረሰውን ኳስ አሜ ወደ ጎል መትቶት የነበረ ቢሆንም ኳስ የግቡን ቋሚ ታካ ወጥታለች፡፡ ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ በጅማ የግብ ክልል ትይዩ አሌክስ አሙዙ አቡበከር ሳኒ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ፍሬው ሰለሞን በቀጥታ መቶ ጥቃት የፈፀመ ሲሆን ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑሪ ኳሱን በሚገርም ብቃት አውጥቶበታል፡፡

ለመከላከሉ ቅድሚያ ሰጥተው በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሲያስቡ የነበሩት ጅማ አባ ጅፋሮች ተመስገን ደረሰ እና ራሂም ኦስማኖን ያማከለ አጨዋወት በመከተል ጨዋታውን ቀጥለዋል። በዚህ አጨዋወትም በ18ኛው ደቂቃ ላይ ራሂም ኦስማኖ ኳስን ከመረብ ቢያዋህድም ከጨዋታ ውጪ ተብላ ግቧ ተሽራለች፡፡ በሂደት ደቂቃ እየገፋ ሲመጣ በእንቅስቃሴ ካልሆነ በቀር በሙከራ ረገድ እየወረዱ የመጡት ወልቂጤ ከተማዎች በመከላከሉ ላይ በሚስተዋልባቸው ክፍተቶች በፈጣኖቹ የጅማ አጥቂዎች ሲፈተኑ ተመልክተናል፡፡ 35ኛው ደቂቃ ኤልያስ አታሮ በግራ በኩል በረጅሙ ወደ ግብ ክልል ሲያሻማ ልማደኛው ተመስገን ደረሰ በግንባር ገጭቶ የነበረ ሲሆን ነገር ግን ኳስ በላይኛው የግቡ ቋሚ ብረት ወጥታለች፡፡ በተመሳሳይ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ራሂም ኦስማኖ ነፃ አቋቋም ለነበረው ተመስገን ደረሰ ሰጥቶት ተጫዋቹ ከጀማል ጣሰው ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ መረጋጋት ተስኖት ወደ ላይ የሰደዳት አጋጣሚም ለቡድኑ አስቆጪዋ ሙከራ ነበረች፡፡ አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሦስት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩ ወልቂጤ ከተማዎች ወደ ጨዋታ ቅኝት በመግባት ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ መድረስ ቢችሉም ጎል ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ አጋማሹም ያለ ጎል ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ብርቱ ፉክክር ማሳየት የቻሉ ሲሆን ወልቂጤ ከተማ ግን በአንፃራዊነት ብልጫ ወስዶ መጫወት ችሏል። ጅማ አባጅፋሮች በበኩላቸው በመልሶ ማጥቃት ጥሩ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሲጥሩ ታይቷል፡፡ አጋማሹ እንደተጀመረም ፍሬው ሠለሞን በቀኝ በኩል ለነበረው አህመድ ሁሴን ሰጥቶት አጥቂው ወደ ሳጥን ሁለቴ ብቻ ገፋ አድርጎ ወደ ጎል የመታው ኳስ በአባጅፋር ተከላካዮች ርብርብ ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡

በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ቢበለጡም በመልሶ ማጥቃት እና ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች የግብ አጋጣሚን ለማግኘት ያልቦዘኑት አባ ጅፋሮች መላኩ ወልዴ ለማሻማት ወደ ግብ የላካት እና ጀማል ጣሰው ለጥቂት በፈጠረው ዝንጉነት በራሱ ላይ ለማስቆጠር ባደረገው ቅፅበታዊ ሙከራ ወደ ወልቂጤ የግብ ክልል ደርሰዋል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ አህመድ ሁሴንን በደንብ ለመጠቀም ያሰቡ ይመስሉ የነበሩት ወልቂጤዎች ያገኙ የነበሩትን የቅብብል ኳሶች ወደ ተጫዋቹ ቶሎ ቶሎ በመላክ ጎል ለማግኘት ታትረዋል፡፡ አህመድ ሁሴን በቀኝ በኩል መትቶ አቡበከር ኑሪ ያዳነበት እና ከቅጣት ምት አሁንም አህመድ አክርሮ መትቶ አቡበከር በድጋሚ የያዘበት ተጠቃሾቹ የቡድኑ ሙከራዎች ናቸው፡፡

የወልቂጤን የመከላከል ድክመት በረጃጅም እና በተሻገሪ ኳሶች ለማስከፈት ሲጥሩ የነበሩት ጅማዎች 77ኛው ደቂቃ ላይ የሚያስቆጭ የግብ አጋጣሚን አግኝተዋል፡፡ ተመስገን ደረሰ ብልጠቱን ተጠቅሞ የሰጠውን ራሂም ኦስማኖ አክርሮ ሞክሮ ጀማል ጣሰው ሲተፋው በድጋሚ ፕሪንስ ዋአንጎ አግኝቶ ቢመታውም ጀማል ጣሰው በሚገርም ብቃት አውጥቶበታል፡፡

የመጨረሻዎቹን አምስት የጭማሪ ደቂቃዎች ወልቂጤ ከተማዎች በተደጋጋሚ ጥቃት ለመሰንዘር ሞክረዋል። በጭማሪ ደቂቃም ሄኖክ አየለ ለአሜ መሐመድ ሰጥቶት ተጫዋቹ ያልተጠቀመባት የመጨረሻ ዕድል የምታስቆጭ ነበረች፡፡ በዚህ መልኩ ጨዋታው ግብ ሳይቆጠርበት ያለ ጎል ተጠናቋል፡፡