የአሠልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 1-0 ኢትዮ ኤሌክትሪክ

በአዳማ ከተማ አንድ ለምንም አሸናፊነት ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ አሠልጣኞች ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየት ሰጥተዋል።

ዘርዓይ ሙሉ – አዳማ ከተማ

ስለ ጨዋታው?

ተጋጣሚያችንን ከዚህ በፊት አላየሁትም ነበር። 10 እና 15 ደቂቃም ለማየት ሞክሬያለሁ። እነሱ ኳስ ይዘው ስለሚጫወቱ ይዘነው የገባነውን ነገር መከተል አልቻልንም። በተለይ ፊት አካባቢ መጀመሪያ አካባቢ ስናገኝ የነበረውን ነገር የመጠቀም አለመቻላችን ጫና ውስጥ እንድንገባ አድርጎናል። እንቅስቃሴው መጥፎ ባይሆንም ፊት ላይ የአጨራረስ ድክመት ይታይብን ነበር። ቀጣይ እዚህ ክፍተት ላይ እንሰራለን።

ስለ ዛሬው ድል?

ለቀጣይ እጅግ በጣም ያነሳሳናል። በእነደዚህ አይነት ውድድር ላይ ሦስት ነጥብ ይዘህ መጀመር እጅግ በጣም ወሳኝ ነው። ከዚህ ውጪ ከከፍተኛ ሊጉ የመጡት ክለቦች ጠንካራ ክለቦች ናቸው ብዬ አስባለው። እኛም በዚህ መንገድ መዘጋጀት አለብን። ከዚህ በኋላ ያሉት እያንዳንዱ ጨዋታዎች የዋንጫ ጨዋታዎች ያክል ናቸው። ስለዚህም ነው የዛሬው ሦስት ነጥብ ወሳኝ ነው የምለው። ተጫዋቾቼም ይሄንን ነጥብ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ነበር። በዚህም በጣም ደስ ብሎኛል።

ክፍሌ ቦልተና – ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ስለ ጨዋታው?

ጨዋታውን እረፍት ላይ መጨረስ ነበረብን። ግን የአጨራረስ ችግር ነበረብን። ይህ ባይሆን ኖሮ 3-0 እረፍት እንወጣ ነበር። ግን እንዳልኩት ብዙ ኳሶችን አባከንን። ይሄ ደግሞ ዋጋ አስከፈለን። በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የነበረንን ብልጫ አይተካል። በዛሬው ጨዋታ መሸነፍ አይገባንም ነበር። በዚህም ደግሞ በጣም አዝኛለሁ።

ረጅም ጊዜ አርራችሁ መምጣታችሁ ተፅዕኖ ፈጥሮባችኋል?

አዎ። ተፅዕኖ ፈጥሮብናል። በአካል ብቃቱ ረገድ ትንሽ ክፍተት ነበረብን። በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙ እያጠቃን ነበር። ከእረፍት በኋላ ግን መዳከሞች ይታዩ ነበር። ከወር በላይ አርፈም የ10 ቀን ዝግጅት ብቻ ነው ያደረግነው። አዳማዎች ግን ውድድር ጨርሰው 10 ቀን ሳያርፉ ነው ዝግጅት የጀመሩት። የአካል ብቃታቸውንም አይተካል። ከዚህም መነሻነት በሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ አልተጫወትንም።