ከዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ከአሰልጣኞች ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገናል።
አሰልጣኝ መሐመድ ኑር – ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከ
ከሜዳ ውጪ ቡድኑ ላይ ተፈጠረ ስለተባለው ጫና መቀየር
ከተጫዋቾች ጋር ሜዳ ላይ ጥሩ ነገር ከሰሩ በቀጣይ የትኛውም ክለብ ተሻምቶ እንደሚወስዳቸው በማግባባት ለዚህ ጨዋታ ዝግጁ እንዲሆኑ ማድረግ ችለናል። በተጨማሪም የክለባችን አመራሮች በትናንትናው ዕለት ቡድኑን በማነሳሳታቸው ሜዳ ላይ ውጤቱን አግኝተናል።
ቡድኑ በቶሎ ወደ ጨዋታ ምት ስለመመለሱ
ሊጉ ላይ ካየሁት ጠንካራው ቡድን መብራት ኃይል ነው። ፈልገው የነበረው ሜዳቸው ላይ ኳሱን ይዘው እኛን ስበውን በመልሶ ማጥቃት መጠቀም ነበር። ለተጨዋቾቼ ይህ እንዳይሆን ነግሬያቸው በተረጋጋ መንፈስ ከሚሳሳቱት ኳስ አግኝተው እንዲጠቀሙ ነበር ዕረፍት ላይ የነገርናቸው ፤ ያንን ተግባራዊ አድርገዋል። እንቅስቃሴው እንደሌላው ጊዜ ፍሰት አልነበረውም ግን ውጤቱን ስለፈለግነው ትኩረታችን እሱ ላይ ነበር።
አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና – ኢትዮ ኤሌክትሪክ
በሁለቱም አጋማሾች መጀመሪያ የነበራቸው ብልጫ በተጋጣሚ ስለመቀልበሱ
የነበረን ከፍተኛ የማሸነፍ ፍላጎት ጫና አድርሶብናል። በግልም በቡድንም እንደሌላው ጊዜ አልነበርንም። ተጋጣሚያችን ደግሞ በቡድን ደረጃ የተሻለ ነበር። በሥነ ልቦናውም ተከላክሎ መልሶ በማጥቃቱም የተሻለ ነበር። እኛ ስህተት እንሰራ ነበር ፤ ሁለተኛውም ግብ በዚያ መልክ የተቆጠረ ነበር። ነቅለን እናጠቃ ነበር። ያ ነገር ጫና ፈጥሮብናል ምንምን ማድረግ አይቻልም ፤ መቀበል ነው።
ይህ ችግር በቀጣይ ጨዋታ ስለሚስተካከልበት መንገድ
አንዳንድ ለውጦች እናደርጋለን። የመጀመሪያ ጨዋታ ላይ ተሸንፈን ነበር ከዛ አሸነፍን። ዛሬም ተቀይረው የገቡ ልጆች የተሻለ ተንቀሳቅሰዋል በቀጣይ የደከሙትን አስቀምጠን ደግሞ ተመጣጣኝ ተጫዋቾችን በማስገባት ለማሸነፍ እንጥራለን።