የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለ2014 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የትግራይ ክልል ክለቦች የማይሳተፉ ከሆነ እነሱን ለመተካት በሀዋሳ እያደረገ ያለው ውድድርን ግምገማ ዛሬ አካሄደ።
በ2014 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ላይ የትግራይ ክልል ሶስቱ ክለቦች የማይሳተፉ እና በቀነ ገደቡ ተገኝተው ካልተመዘገቡ እነርሱን ለመተካት በሁለተኛ አማራጭነት የተቀመጠው የሟሟያ ውድድር ከፕሪምየር ሊግ በወረዱት ወልቂጤ ከተማ፣ ጅማ አባጅፋር እና አዳማ ከተማ እንዲሁም ከከፍተኛ ሊግ ሦስቱ ምድቦች ሁለተኛ ሆነው በጨረሱት ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ሀምበሪቾ ዱራሜ እና ኮልፌ ቀራኒዮ መካከል በሀዋሳ ከተማ ከሰኔ 18 ጀምሮ ጨዋታ እየተደረገ ይገኛል። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን እና በፕሪምየር ሊጉ ሼር ካምፓኒ አማካኝነት እየተካሄደ ሦስተኛ የዙር ጨዋታ ላይ የደረሰው ይህ ውድድር በዛሬው ዕለት ግምገማ እና ውይይት በሀዋሳ ሴንትራል ሆቴል ላይ ከአዳማ ከተማ ክለብ ተወካይ በስተቀር የአምስቱ ክለቦች ቡድን መሪ እና አሰልጣኝ በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ ዶ/ር ወገኔ ዋልተንጉሥ (የዚህ የማሟያ ውድድር ም/ሰብሳቢ) ስለተደረጉት ሦስት ዙር ጨዋታዎች ሪፖርት ለተገኙት ክለቦች አቅርበዋል፡፡ ም/ሰብሳቢው ባቀረቡት ሪፖርት የተመዘገቡ ውጤቶች እና ቁጥራዊ መረጃዎች ጠቅሰው የአንድ የክለብ አመራር ባሰየው የስነ ምግባር ጥሰት የተቀጣ መሆኑን፣ ሦስት የዲሲፕሊን ጥሰት የታየባቸው ተጫዋቾች በምክር እንደታለፉ ገልጸዋል፡፡ “እንዲህ አይነት ውይይቶች በጣም አስፈላጊ ናቸው። ለአንድ ውድድር ጠንካራ እና ደካማ ጎኖችን ማወቅ የሚቻለው በዚህ አይነት ስብሰባዎች በመሆናቸው ሁሉም ይሄን ልማድ መልመድ አለበት። በተለይ የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ፕሪምየር ሊግ ካሉ ክለቦች ጋር ልምድ ለማግኘት እንዲህ አይነት መድረክ አስፈላጊ ነው።” በማለት አክለዋል፡፡
በመቀጠል በውይይቱ እና ግምገማው ላይ የተገኙት ክለቦች ተመሳሳይ ይዘት ያለው ቅሬታ እና ጥያቄ ለውድድሩ አመራሮች አቀርበዋል፡፡ የክለብ ቡድን መሪዎች በዋናነት “የመለማመጃ ሜዳ ቀድሞ አልተዘጋጀልንም፤ በበቂ ሁኔታም እያገኘን አይደለም፣ ወቅቱ የኮቪድ ቢሆንም ደጋፊዎች ወደ ስታዲየም ያለ አግባብ እየገቡ ነው። ከዚህ ባለፈ ደጋፊ የሌለንን ክለቦች እየጎዳን ነው፣ የኳስ አቀባዮች በአግባቡ አለመኖራቸው የሰዓት መዘግየቶችን እያስከተለ ነው፣ ዳኞች ተጫዋቾችን የሚመዘግቡበት ወረቀት የስም መፃፊያው በቁጥር የተገደበ በመሆኑ በወረቀቱ ላይ የይዘት ማሻሻያ ይደረግበት፣ የመጨረሻ ጨዋታ ላይ ተቀራራቢ ውጤት ያላቸው ቡድኖች በዕኩል ሰዓት ጨዋታ እንዲያደርጉ ምን ታስቧል?…” በማለት የጠየቁ ሲሆን በአንድ ድምፅ ተሰብሳቢዎቹ ዳኝነቱ መልካም በመሆኑ አመስግነዋል፡፡
በመጨረሻም በተነሱ ጥያቄዎች ላይ ሻምበል ሀለፎም ህሩይ (የውድድሩ ሰብሳቢ) እና ዶ/ር ወገኔ ዋልተንጉስ ምላሽን ሰጥተዋል፡፡ ሻምበል ሀለፎም “ከጊዜ መጠባብብ ጋር በተያያዘ በበቂ ሁኔታ ተዘጋጅተናል ማለት ይከብዳል። ቢሆንም ውድድሩ ከሞላ ጎደል ጥሩ እየሄደ ነው። ከልምምድ ሜዳው ጋር አያይዛችሁ ያነሳችሁትን እኔም እቀበለዋለሁ። ከነገ ጀምሮ ግን ይሄን ለመቅረፍ ከሜዳ አዘጋጅ ኮሚቴዎች ጋር ስለተነጋገርን ይፈታሉ ብለን እናምናለን። ሌላው በዳኝነቱ ላይ እንዳላችሁት የተነሱ ቅሬታዎች ብዙም የሉም በጥሩ መልኩ እየሄዱ ስለሆነ እኛም በግምገማችን መልካም ነው ብለን አልፈነዋል።” ብለዋል፡፡
ዶ/ር ወገኔ ቀጥለው ስለ ደጋፊ እንዲሁም ተቀራራቢ ነጥብ ያላቸው ክለቦች በመጨረሻ ጨዋታቸው በተመሳሳይ ሰዓት መጫወት አለባቸው ስለተባሉ ጉዳዮች መልስ ሰጥተዋል፡፡ “በእርግጥ ከደጋፊዎች ጋር ያነሳችሁት ጥያቄ አግባብነት አለው። በዚህ ውድድር ላይ ደጋፊዎች መግባት የለባቸውም የሚል አቋምን ወስደናል። ከቢሮ ባለሙያ እና ክለቡን ከሚመለከታቸው አመራሮች ውጪ ማንም አይገባም። እናንተ ክለቦች ከጨዋታ አንድ ቀን ቀደም ብላችሁ አስር የሚሆኑ የናንተን አመራር ብቻ ስም ዝርዝር ስጡን። በሱ መሠረት ስም እየጠራን እናስገባለን። ከዛ ውጪ ማንም ደጋፊ ወደ ሜዳ መግባት አይችልም። ስለ ኳስ አቀባይ የተነሳውን ተቀብለናል። በቀጣይ አስተካክለን እንገኛለን። በመጨረሻ መናገር የምፈልገው ተቀራራቢ ነጥብ ያላቸውን ክለቦች ይመለከታል። ይሄ ጥያቄ አግባብ እንደሆነ እኛም ቀድመን ያቀድነው ዕቅድ ነው፡፡በቀጣይ ረቡዕ በሚኖረው ጨዋታ ተቀራራቢ ውጤት ያላቸው ይለያሉ። እነሱን ቀድመን ከለየን በኃላ የመጨረሻ ጨዋታቸውን በዕኩል ሰአት ማድረግ ስላለባቸው በየትኛውም ሜዳ ይጫወቱ የሚለውን በዕጣ እንለያለን። ያን ካደረግን በኃላ ጨዋታዎቹ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እና በአርቴፊሻል ሜዳ ላይ በዕጣው መሠረት ክለቦቹ ይጫወታሉ።” በማለት አብራርተዋል።
ከዳኞች ኮሚቴ የተወከሉት አቶ ኃይለመላክ ተሰማ የስም ዝርዝር መፃፍያ ቅፁ ስም ለመፃፍ በቂ ቦታ የለውም ስለ ተባለው ጉዳይ ፎርሙ የሚዘጋጀው በፌዴሬሽኑ በመሆኑ እዚህ ላይ ማሻሻያ እንደማይኖረው ገልፀው ከጀርባ ባለው ባዶ ቦታ የቀረ ስም ዝርዝር ካለ መፃፍ እንደሚቻል ገልፀው ፕሮግራሙ ተገባዷል፡፡