በዘንድሮ የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላለመውረድ ሲፎካከር የነበረው ሲዳማ ቡና በቀጣይ ዓመት ተጠናክሮ ለመቅረብ በዝውውር ገበያው ላይ ተሳትፎ ማድረግ ጀምሯል።
የ2013 ቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመንን በአስቸጋሪ ሁኔታ አሳልፎ ከመውረድ በመጨረሻዎቹ የሊጉ ሳምንታት የተረፈው ሲዳማ ቡና ለቀጣዩ የ2014 የውድድር ዘመን ጠንካራ እንዲሁም የዋንጫ ተፎካካሪ ሆኖ ለመገኘት የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌን ኮንትራት ለማራዘም በድርድር ላይ የሚገኝ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ ግብ ጠባቂ ለሁለት ዓመት ማስፈረሙ ተረጋግጧል።
የቀድሞው የሀላባ ከተማ፣ አዲስ አበባ ከተማ እንዲሁም ሀዋሳ ከተማ ግብ ጠባቂ የነበረው እና የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ተክለማርያም ሻንቆ በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌው ኢትዮጵያ ቡና ያለፉትን ሁለት የውድድር አመት በመጫወት ካሳለፈ በኃላ በዛሬው ዕለት በይፋ ሌላኛው በቡና ስያሜ የሚጠራውን የክልል ክለብ ሲዳማ ቡናን ተቀላቅሏል፡፡
ክለቡ በዚህ ሳምንት የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌን ውል ጨምሮ አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማስፈረም በሂደት ላይ እንዳለ የክለቡ አዲሱ ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ ተስፋዬ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡