ዛሬ ረፋድ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ያደረገው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ነገ ወደ ባህር ዳር ከማምራቱ በፊት ምሽት ላይ አሸኛኘት ተደርጎለታል።
በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከፊታችን ቅዳሜ ጀምሮ በሚደረገው የምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ ጠንካራ ሆኖ ለመቅረብ ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል። በሳምንቱ አጋማሽ ከኢትዮጵያ መድህን ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ ያደረገው ብሔራዊ ቡድኑም ዛሬ ረፋድ ወደ አዳማ በማቅናት ሌላ የአቅም መፈተሻ ጨዋታ ከአዳማ ከተማ የወጣት ቡድን ጋር አድርጓል። በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በተከናወነው ጨዋታ ላይ ፅዮን መርዕድ፣ ኃይሌ ገብረትንሳኤ፣ ሠለሞን ወዴሳ፣ መናፍ ዐወል፣ ዩሃንስ ሰጌቦ፣ ሐብታሙ ተከስተ፣ ዊሊያም ሠለሞን፣ አብዱልሃፊዝ ቶፊቅ፣ ቸርነት ጉግሳ፣ አቡበከር ናስር እና ብሩክ በየነ በቋሚነት ተሰልፈው ነበር።
በጨዋታው ላይ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ስንታየሁ መንግስቱ፣ ዱሬሳ ሹቢሳ፣ ሙኧዲን ሙሳ፣ ወንድማገኝ ማርቆስ፣ በረከት ወልዴ እና እያሱ ለገሠ ቀይረው አስገብተው ጨዋታውን ጨርሰዋል። ለ90 ደቂቃዎች በተከናወነው ጨዋታ ላይም ብሔራዊ ቡድኑ በአቡበከር ናስር፣ አብዱልሃፊዝ ቶፊቅ፣ ዊልያም ሠለሞን፣ ሙኧዲን ሙሳ፣ ስንታየሁ መንግስቱ፣ ቸርነት ጉግሳ እና ኃይሌ ገብረትንሳኤ አማካኝነት ከግማሽ ደርዘን በአንድ የበለጠ ጎሎችን አስቆጥሯል።
ብሔራዊ ቡድኑን ከትናንት በስትያ የተቀላቀሉት ግብ ጠባቂው ታምራት ዳኜ እና የመስመር ተከላካዩ አስራት ቱንጆ እንዲሁም ትናንት ስብስቡን የተቀላቀለው መሳይ ጻውሎስ በዛሬው ጨዋታ ላይ ተሳትፎ አልነበራቸውም ነበር። የብሔራዊ ቡድኑ አባላት እኩለ ቀን ጨዋታውን ከጨረሱ በኋላም እዛው አዳማ ምሳ ተመግበው 11 ሰዓት ላይ ወደ አዲስ አበባ አዲስ አበባ ገብተዋል።
በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ እግርኳስ ደጋፊዎች ማኅበር ምሽት ላይ ቡድኑ ወደሚገኝበት የካፍ የልዕቀት ማዕከል በማምራት የአሸኛኘት ሥነ-ስርዓት እንዳደረገለት ሰምተናል። የማኅበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ምንያህል ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ከሆነ የማኅበሩ አመራሮች እና አባላት ስፍራው ተገኝተው የኬክ ቆረሳ መርሐ-ግብር አከናውነዋል። ከኬክ ቆረሳው መርሐ-ግብር በኋላ ብሔራዊ ቡድኑን ወክለው አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ለተደረገላቸው ነገር አመስግነው የሀገራቸውን ባንዲራ ከፍ ለማድረግ እንደሚጥሩ ተናግረዋል። አሠልጣኙ አያይዘውም ከተለያየ ክለብ የመጡት ደጋፊዎች ቡድኑን በአንድነት እንዲደግፉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ነገ ከሰዓት ውድድሩ ወደሚደረግበት ባህር ዳር ከተማ እንደሚያቀና ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።