በዝውውር ገበያው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በዛሬው ዕለት የመሐል ተከላካያቸውን ውል አራዝመዋል።
አንጋፋው የፕሪምየር ሊጉ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀጣይ የውድድር ዓመት ተጠናክሮ ለመቅረብ ቅድመ ሥራዎችን እየከወነ እንደሚገኝ ይነገራል። ከትናንት በስትያ የጋቶች ፓኖምን ዝውውር የፈፀመው ክለቡ በዛሬው ዕለት ደግሞ የነባር ተጫዋቾችን ውል ማደስ መጀመሩን ሶከር ኢትዮጵያ ተረድታለች። ውሉን ያደሰው ተጫዋች ደግሞ የመሐል ተከላካዩ ሳላዲን በርጌቾ ነው።
ከስምንት ዓመታት በፊት ከኢትዮጵያ መድህን ቅዱስ ጊዮርጊስን የተቀላቀለው ሳላዲን ከክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ አልፎ ሀገሩን ሲያገለግል እንደነበረ ቢታወቅም በተለያዩ ጊዜያት የሚያጋጥሙት ጉዳቶች በወጥነት እንዳይጫወት አድርጎታል። ዘንድሮም በታሰበው መንገድ ክለቡን ማገልገል ሳይችል ቀይቶ በመጨረሻዎቹ የሊግ ጨዋታዎች ላይ ወደ ሜዳ መመለሱ ይታወሳል። ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታትም ከፈረሰኞቹ ጋር ያለውን ቆይታ ማራዘሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።