በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ጠንካራ ተፎካካሪ የሆነው ሀዋሳ ከተማ አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የሦስት ነባሮችን ውልም አድሷል፡፡
ክለቡን የተቀላቀለችው የመጀመሪያዋ ተጫዋች ብዙሀን እንዳለ ሆናለች፡፡ የቀድሞዋ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አምበል እና አማካይ ያለፉትን ዓመታት በድሬዳዋ ቆይታ ያደረገች ሲሆን አሁን ደግሞ ወደ ሀዋሳ አምርታለች፡፡
ሌላኛዋ ፈራሚ ተከላካዩዋ ማኅደር ባዬ ነች። የዐፄዎቹ ተከላካይ ያሬድ ባዬ እህት የሆነችው ማኅደር በዳሽን ቢራ፣ ጥረት ኮርፖሬት እንዲሁም ያለፉትን ሁለት የውድድር ዓመታት በድሬዳዋ ከተማ አሳልፋ ከቆየች በኀኋላ ማረፊያዋን ሀዋሳ አድርጋለች፡፡
ሦስተኛ ፈራሚ ፈጣኗ አጥቂ ቁምነገር ካሣ ሆናለች፡፡ በኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም ከ2012 ጀምሮ ደግሞ በድሬዳዋ ከተማ ቆይታ የነበራት ተጫዋቿ የቡድን አጋሮቿን ተከትላ ወደ ክለቡ አምርታለች፡፡
አራተኛዋ ፈራሚ መንደሪን ክንዲሁን ነች። አማካይዋ ምርጥ የውድድር ዓመትን በማሳለፍ ጌዲኦ ዲላን በአምበልነት ስትመራ የነበረ ሲሆን በቀጣይ በሀዋሳ መለያ ለመታየት ለክለቡ ፊርማዋን አኑራለች፡፡
ከአዳዲስ ፈራሚዎቹ በተጨማሪ የአጥቂዋ ነፃነት መናን እንዲሁም የአማካዩቹ ዙፋን ደፈርሻ እና ቅድስት ቴቃን ውል ለሁለት ተጨማሪ ዓመት ማራዘሙን ክለቡ በይፋ ማስፈረሙን ሶከር ኢትዮጵያ በስፍራው በመገኘት አረጋግጣለች፡፡