የኢትዮጵያ እግርኳስ ተጫዋች ሙያተኛ ማኅበር በአውሮፓ ከሚገኝ ፌዴሬሽን ጋር አብሮ ለመሥራት መስማማቱ የሚታወቅ ሲሆን አሁን ደግሞ አሜሪካ ካለ የስፖርት እና ባህል ማኅበር ጋር አብሮ ለመስራት ያደረገው ውይይት ፍሬ አፍርቷል።
ከሁለት ዓመት ያልዘለለ ዕድሜ ያለው የኢትዮጵያ እግርኳስ ተጫዋቾች ሙያ ማኅበር (የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ፉትቦለርስ አሶሴሽን) የአባላቱን መብት በማስጠበቁ ረገድ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሰራ ይታያል። ከዚህ ተጨማሪ ከተለያዩ በስፖርቱ ውስጥ ከሚገኙ ተቋማት ጋር አብሮ ለመስራት እየተንቀሳቀሰ እንደነበር ሲገልፅ የነበረው ማኅበሩ በአውሮፓ እና አሜሪካ ካሉት የስፖርት እና ባህል ፌዴሬሽኖች ጋር ማንኛውንም የሙያ እና የአቅም ድጋፍ ለማግኘት እንዲሁም በጋራ አብሮ ለመስራት መስማማቱን ለሶከር ኢትዮጵያ አስረድቷል።
በ2003 የተቋቋመው እና በአውሮፓ መቀመጫውን ያደረገው የኢትዮጵያን የባህል እና የስፖርት ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ፉትቦለርስ አሶሴሽን የላከለትን የአብረን እንስራ ጥያቄ መቀበሉን በይፋዊ ደብዳቤው መቀበሉን ማረጋገጡ ይታወሳል።
በዋናነት ደግሞ ፌዴሬሽኑ በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ውስጥ የራሳቸውን አሻራ አሳርፈው ያለፉ እና ለብሔራዊ ሰንድቅ አላማቸው በስፖርቱ ዘርፍ ብዙ መስዋዕትን የከፈሉ ግን አስታዋሽ አጥተው የማይገባቸውን ሕይወት እየኖሩ የሚገኙ የቀድሞ ተጫዋቾችን መደገፍ እና ላበረከቷቸው አስተዋጽዎች ተገቢውን እውቅና መስጠት እንዲሁም አሁን በመጫወት ላይ ያሉ ስፖርተኞች ለሙያቸው ተገቢውን ክብር እንዲሰጥ ከማኅበሩ ጋር እንደሚሰራ ገልጿ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ በእግርኳሱ ዘርፍ ያሉ ሙያተኞች ክህሎታቸው እንዲዳብር እና ዓለም ያለበትን የእግር ኳስ ደረጃ እንዲሁም የስልጠና አሰጣጣቸው ዘመኑን የተከተለ እና ሳይንሱን ያማከለ እንዲሆን በየደረጃው የሚሰጡ ስልጠናዎች ከማኅበሩ ጋር እየተነጋገረ እንዲሰጥ እንደሚያደርግ በደብዳቤ አያይዞ ነበር።
አሁን ደግሞ የሰሜን አሜሪካው የኢትዮጵያዊያን ስፖርት እና ባህል ማኅበር ፕሮፌሽናል ፉትቦለርስ አሶሴሽኑ ለኢትዮጵያውያን እግር ኳስ ተጫዋቾች እና ለስፖርቱ ጠቅላላ ዕድገት ለሚያደርገው ድጋፍ ምስጋና እንዳለው ገልጾ አቅሙ በፈቀደው እና በሚችለው መንገድ ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል። በተጨማሪም ማኅበሩ የተዘጋጀባቸው ሥራዎች ሙሉ ለሙሉ እንዲከናወኑ የኢትዮጵያ ስፖርት እና ባህል ሚኒስትር፣ የከተማ አስተዳደሮች፣ የኢትዮጵያውያን ስፖርት ተቋማትና ደጋፊዎቻችው እንዲሁም የሚመለከታቸው እና ኃላፊነት የተሰጣቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት አስፈላጊውን ትብብር ለማኀበሩ እንዲያረጉ አሳስቧል።