ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሰው መከላከያ የዋና እና ምክትል ኮንትራት ሲያድስ ሁለት ተጨማሪ ረዳት አሰልጣኞችንም ቀጥሯል፡፡
‘ጦሩ’ በ2011 ከሊጉ ከወረደ በኃላ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በከፍተኛ ሊጉ ላይ ሲወዳደር ቆይቶ ዘንድሮ በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ እየተመራ በከፍተኛ ሊጉ የምድብ ሀ አሸናፊ በመሆን በድጋሚ ወደ ፕሪምየር ሊጉ መመለሱን ማረጋገጡ ይታወሳል፡፡ በቀጣዩ ዓመት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ የሆነው ክለቡ የአሰልጣኝ ቡድን አባላትን በማስፋት በዛሬው ዕለት የአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ እና ዮርዳኖስ ዓባይን ውል ሲያራዝም አምሳሉ እስመለዓለም እና በለጠ ወዳጆን በአሰልጣኝ ቡድኑ ውስጥ ቀላቅሏል፡፡
የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንዲሁም የደደቢት፣ መቐለ 70 እንደርታ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ አሰልጣኝ የነበሩት ዮሐንስ ሳህሌ ዘንድሮ መከላከያን ከከፍተኛ ሊጉ ወደ ፕሪምየር ሊጉ መመለስ በመቻላቸው ለአንድ ተጨማሪ ዓመት የክለቡ ቦርድ ቆይታ እንዲኖራቸው በወሰነው ውሳኔ መሠረት ክለቡን በ2014 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለመምራት ፊርማቸውን ማኖራቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ አረጋግጣለች። አሰልጣኙ ከዋና አሰልጣኝነት በተጨማሪም መከላከያ በሁለቱም ፆታ ሆነ በታዳጊ ቡድኑ ላይ ያሉ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን በዋናነት ደርበው እንዲሰሩም ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡
ከዋና አሰልጣኙ በተጨማሪ የቀድሞው አጥቂ ዮርዳኖስ ዓባይ ዋናው አሰልጣኝ አብሯቸው እንዲዘልቅ ለክለቡ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት በቀጣዩም ዓመት በረዳት አሰልጣኝነት እንደሚቀጥል ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡
ከሁለቱ አሰልጣኞች በተጨማሪ መከላከያ ሁለት ተጨማሪ የአሰልጣኝ ቡድን አባላትን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል፡፡የባህርዳር ከተማ የተስፋ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩት አምሳሉ እስመለዓለም ሌላኛው የመከላከያ አዲስ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን ሲሾም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ20 ዓመት በታች እና የወልቂጤ ከተማ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ የነበረው በለጠ ወዳጆ በድጋሚ ወደ ቀድሞ ክለቡ መከላከያ በመመለስ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ በመሆን ተሹሟል፡፡
በዚህ መልኩ የአሰልጣኝ ቡድኑን ያዋቀረው ጦሩ ወደ ተጫዋቾች የዝውውር ገበያ በቅርቡ እንደሚገባም አረጋግጠናል፡፡