ቻምፒየንስ ሊግ፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚ ቲፒ ማዜምቤ በሳምንቱ መጨረሻ ድል ቀንቶታል 

የወቅቱ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ እና ሱፐር ካፕ አሸናፊ የዲ.ሪ. ኮንጎው ቲፒ ማዜምቤ በኮንጎ ሱፐር ሊግ ዕሁድ በተደረገ ጨዋታ ሴንት ሉፖፖን 2-0 አሸንፏል፡፡

ዓምና በኤስ ቪታ ተቀድሞ የሊጉን ክብር ያጣው ማዜምቤ ሴንት ሉፖፖን በጆናታን ቦሊንጊ ሁለት ግቦች ታግዞ ማሸነፍ ችሏል፡፡ የኮንጎው አጥቂ ቦሊንጊ በዘጠኝ ደቂቃዎች ውስጥ ያስቆጠራቸው ሁለት ግቦች የሉቡምባሺውን ክለብ አሸናፊ ለማድረግ በቂ ነበሩ፡፡ ጋናዊው ሰለሞን አሳንቴ እና የመስመር ተከላካዩ ካቦሶ ለግቦቹ መገኘት ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል፡፡ የማዜምቤ አምበል እና የረጅም ግዜ ተመራጭ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኪዲያባ ጨዋታውን በተለዋጭ ወንበር ላይ ተቀምጧ ለማየት ተገዷል፡፡

አሰልጣኝ ቬሉድ ሁበርት ሮጀር አሳሌ፣ ቶማስ ኦሊሜዎንጉ እና ዳንኤል አዴጂ በጨዋታው ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ሳያስገቡ ጨዋታውን ጀምረዋል፡፡

ቦሊንጊ ሩዋንዳ ባዘጋጀችው የቻን ዋንጫ ሻምፒዮን የነበረው የኮንጎ ብሄራዊ ቡድን አባል ሲሆን በውድድር ዘመኑ የማዜምቤን የፊት መስመር በመምራት ላይ ይገኛል፡፡

ማዜምቤ የፊታችን ዕሁድ በባህርዳር ስታዲየም በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የመጀመሪያው ዙር ማጣሪያ ቅዱስ ጊዮርጊስ ይገጥማል፡፡ ፈረሰኞቹ ማክሰኞ ወደ ባህርዳር እንደሚያቀኑ ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *